አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ)የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት )የከፍተኛ አመራሮች ድርጅታዊ ኮንፈረንስ በሚቀጥለው ሳምንት በመቐለ ከተማ እንደሚካሄድ ተገለፀ።
ከጥር 3/2010 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 8 ቀናት በሚካሄደው ሰባተኛው ዙር ድርጅታዊ ኮንፈረንስ፥ ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች የሚታደሙ አመራሮች በእንግዳነት ይሳተፉበታል ተብሏል።
በኮንፈረንሱ 2 ሺህ 500 አመራሮች ይገኙበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተነገረው።
ሰባተኛ ደርጅታዊ ኮንፈረንሱ የጥልቅ ተሃድሶ ሂደቱ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሲሆን፥ በክልሉ እና በሀገሪቱ አንዣቦ ያለው አደጋ በሚገባ ገምግሞ መፍትሄ እና ቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።
በዚህም የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ፥ ድርጅቱ ዳግም ጠንክሮ የሚወጣበት ታሪካዊ ኮንፈረንስ እንደሚሆን ይጠበቃል ነው የተባለው።
የህወሓት ስራ አስፃሚ ኮሚቴ በቅርቡ ያካሄደውን ስር ነቀል ግምገማ፣ ሂስና ግለ ሂስን ተከትሎ ዘጠኝ አባላት ያሉት የድርጅቱን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫን ማካሄዱ ይታወቃል።