Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት እንደሚሆኑ ተጠቆመ


ላለፉት በርካታ ዓመታት የፌዴራል መንግሥት ካቢኔ አባልና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ የክልሉ ፓርቲ ሕወሓት መወሰኑን አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገለጹ።

የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰኞ ታህሳስ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በፌዴራልና በክልሉ መንግሥት፣ እንዲሁም በፓርቲ ኃላፊነቶች የሚመደቡ የሥራ አስፈጻሚ አባላቱን ዝርዝር ይፋ አድርጓል።

አምስት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በትግራይ ክልል፣ አራቱ ደግሞ በፌዴራል ደረጃ እንዲሠሩ መወሰኑን የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ መግለጫ ያመለክታል።

በዚህ መሠረት በትግራይ ክልል እንዲሠሩ የተመደቡት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ አዲስ ዓለም ባሌማ (ዶ/ር) እና ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ናቸው።

በሕወሓት ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ኃላፊነቶች ላይ የተመደቡት ደግሞ ቀደም ሲል የሕወሓት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ዓለም ገብረ ዋህድ፣ በፌዴራል መንግሥት የቀድሞ የመንግሥት ጉዳዮች ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የፍትሕ ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ጌታቸው ረዳ ናቸው።

በፌዴራል መንግሥት መዋቅሮች ውስጥ እንዲሠሩ ከተመደቡት መካከል፣ በሕወሓት ጽሕፈት ቤት ውስጥ እያገለገሉ የነበሩትና ሕወሓት በቅርቡ ባካሄደው 35 ቀናት የፈጀ ግምገማ ማገባደጃ ላይ፣ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት በተጨማሪ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ የመረጣቸው ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር ናቸው።

በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት እያገለገሉ የሚገኙ ሦስት የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ በፌዴራል መንግሥት መዋቅር ውስጥ እንዲያገለግሉ ተመድበዋል። እነዚህ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ ያሉት አብረሃም ተከስተ (ዶ/ር) እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ ናቸው።

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ የድርጅቱ ሊቀመንበርና የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑትን አቶ ዓባይ ወልዱን ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነትና ከድርጅቱ ሊቀመንበርነት በማንሳት፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው እንዲያገለግሉ መወሰኑ ይታወሳል። በድርጅቱ አሠራር መሠረት የክልሉ ፕሬዚዳንት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል መሆን የሚጠበቅበት በመሆኑ፣ አቶ ዓባይን ከሥራ አስፈጻሚነትና ከፓርቲው ሊቀመንበርነት በማንሳቱ ከክልል ፕሬዚዳንትነት ሥልጣናቸውም እንደሚነሱ ይጠበቃል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘም ሕወሓት አዲስ የሥራ አስፈጻሚ አባላቱን በፌዴራል፣ በክልልና በፓርቲ ምድቦች ባለፈው ሰኞ ደልድሏል። በትግራይ ክልል እንዲያገለግሉ ከተመደቡት ውስጥ የፓርቲው ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ለክልሉ ፕሬዚዳንትነት ዕጩ ሆነው እንደሚቀርቡ፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የፌዴራል ፓርላማ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የሚመረጠው ደግሞ ከክልሉ ምክር ቤት አባላት መካከል እንደሚሆን የክልሉ ሕገ መንግሥት ይደነግጋል።

በመሆኑም እሳቸው የክልሉ ፕሬዚዳንት ለመሆን የሚጠበቅባቸውን የክልሉ ምክር ቤት አባል የመሆን ሕገ መንግሥታዊ መሥፈርት እንዴት ሊያሟሉ እንደሚችሉ የተጠየቁት እኝሁ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ሕጉን ተከትሎ የተጓደሉ የክልሉ ምክር ቤት አባላትን ለመተካት በሚካሄድ የማሟያ ምርጫ ተሳትፈው የምክር ቤቱ አባል ሊሆኑ እንደሚችሉና ይህ ሒደትም በፍጥነት እንደሚከናወን ገልጸዋል።

የማሟያ ምርጫ የሚካሄደው በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች በተለያዩ ምክንያቶች የተጓደሉ አባሎቻቸው እንዲሟሉላቸው ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ቦርዱ ጥያቄው በቀረበ ሦስት ወራት ውስጥ የማሟያ ምርጫ እንደሚያካሂድ በምርጫ ሕጉ 532/2007 አንቀጽ 29 ሥር ተደንግጓል።

የፌዴራል ፓርላማ ተመራጭ አባል ለአፈ ጉባዔው በማሳወቅ አባልነቱን በገዛ ፈቃዱ መልቀቅ እንደሚችል የሥነ ሥርዓትና የአባላት ሥነ ምግባር ደንቡ ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ከፌዴራል በፓርላማ አባልነታቸው ከመልቀቅ የሚያግዳቸው ነገር አይኖርም።

ከትግራይ ክልል ምክር ቤት የማሟያ ምርጫ ጥያቄ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀርቦ እንደሆነ ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ፣ የቦርዱ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተስፋዓለም ዓባይ እስከ ማክሰኞ ታኅሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ አለመቅረቡን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
Source: Ethiopian reporter