የህወሓት/ ኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ ለላፉት 35 ቀናት ባካሄደው ስብሰባ የድርጅቱ ስትራቴጂካዊ አመራር ክልላዊና ሃገራዊ ተልእኮውን ከመወጣት አንፃር ያለበት ቁመና ለማየት የሚያስችል ስር ነቀል ግምገማ አካሂዷል፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ከመገንባት፤ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ መዋቅራዊ ለውጥ ከማረጋገጥ፣ የህዝባችንን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከመመለስ አንፃር ያሉበት መሠረታዊ ክፍተቶችንና አዲስቷን ፌዴራላዊት ዴሞክሰራሲያዊት ኢትዮጵያ ከመገንባት አኳያ የተጋረጡ አሳሳቢ አዝማሚያዎች በጥልቀት ገምግሟል፡፡ ይህን መሰረት አድርጎ ባደረገው ሂስና ግለሂስ ተከትሎ የእርምት እርምጃ በመውሰድና የአመራር ሽግሽግ በማድረግ ተጠናቋል፡፡
እንደሚታወቀው ሁሉ ህወሓት የትጥቅ ትግል ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በየደረሰበት የትግል ምእራፍ ውስጥ ሁሉ የሚገጥሙትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች በስከነ ሳይነሳዊ ኣመራርና በኣባላቱና በህዝብ የተማላ ተሳትፎ በአስተማማኝ እየመከተ ለድል የበቃ ድርጅት ነው፡፡ የህዝብን ፀረ-ጭቆና፣ ፀረ ኃላቀርነትና ፀረ-ድህነት ትግል ለስኬት ለማብቃት የሚያስችሉ የጠራ መስመር፣ መስመሩን ለማስፈፀም የሚያስችሉ ስትራተጂዎችና ስልቶችን እየቀየሰ ከኣንድ የትግል ምዕራፍ ወደ ሌላው የትግል ምዕራፍ ለመሸጋገር የቻለበት ምስጢር ግልፅ ነው፡፡ ህዝባዊ ወገንተኝነቱ አስተማማኝ የሆነ፣ ፈተናዎች በገጠሙት ቁጥር ራሱን በሚገባ እየፈተሸና ወቅቱ የሚጠብቀውን ፤ ማንኛውንም የእርምት እርምጃ እየወሰደ ጥንካሬዎቹን የሚያጎለብት ድክመቶቹ ያለምህረት በማስወገድ በመስዋእትነት የደመቀ ታሪክ መስራት የቻለ ኣመራር ባለቤት በመሆኑ ነው፡፡
ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ከእህትና አጋር ድርጅቶችና ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን በከፈሉት እጅግ ከባድ መስዋእትነት አዲሱቷን ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ችለዋል፡፡ በአገራችን ታሪክ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የህዳሴ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡
ይሁንና በትጥቅ ትግልም ወቅት ሆነ በልማትና በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንቅስቃሴያዎችን እጅግ የሚያኮራ ተግባራትን የፈፀመ ድርጅት ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ከችግር ኣዙሪት መውጣት አቅቶት የሚንገዳገዱበትና ለህዝብ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ መስጠት ላይ ሰፊ ድክመት እያሳየ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥረዋል፡፡ በተለይም ካለፉት ጥቂት ኣመታት ወዲህ ስትራቴጂካዊ ኣመራሩ እየተዳከመ ተልእኮውን ለመወጣት የሚያስችል ቁመና፣ ኣመለካከትና ኣደረጃጀቱ በየጊዜው እየተሸረሸረ፣ ህዝባዊነቱ እየቀነሰ፣ የህዝብን ችግር በማያወለዳ መልኩ ሳይፈታ በትንንሽ ድሎች የሚረካ ሆኖ በመገኘቱ ምክንያት የመፍትሔ አካል ከመሆን ይልቅ የችግር ምንጭ መሆን የጀመረበት ሁኔታ በስፋት መታየት ከጀመረ ውሎ ኣድራል፡፡ ይህንን ቁመና ይዞ መስመሩንና የመለስን ለጋሲ ማስቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ እንደሌለ በግልፅ አይቷል፡፡
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ማእከላዊ ኮሚቴው ከገባባት ኣዙሪት ለመውጣት ያለው ብቸኛ አማራጭ በድርጅት የቆየ ሳይነሳዊ የትግል ባህልና ታሪክ መሰረት በቁጭት ተነሳስቶ ጥልቀት ያለው የአመራር ግምገማ ማድረግ ብቻ እንደሆነ በማመን በኣፅንኦት መክራል፡፡ ያጋጠሙትን ፈተናዎች በጥሞና መርምሮ ድርጅቱን በማያዳግም ሁኔታ ወደ ትክክለኛው መስመሩና ህዝባዊ ወገንተኝነቱ ለመመለስ በሚያስችለው መልኩ ራሱን በጥልቀት ፈትሿል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ስደረጉ ከነበሩት የይስሙላ ግምገማዎች በዓይነቱና መልኩ በተለየ ችግሮቹን በሚገባ ለመለየት ያስቻሉት መተጋገል አካሂዷል፡፡
ወደ ግምገማ ሲገባ አሁን በስራ ላይ ያለውና ተተኪው አመራር በጋራ ትኩረት ሰጥቶ ያየው ጉዳይ ከገባበት የአመራር አዙሪት ውስጥ ለመውጣት በተለመደው መንገድ መሄድ በፍፁም የማይዋጣ መሆኑን በመገንዘብ ከተለመደው ግምገማ ለመውጣት ያስችላል ተብሎ የታመነበትና ስፋትና ጥልቀት ያለው ክርክር የጋበዘ የድርጅቱን ኣጠቃላይ ሁኔታና የኣመራሩን ድክመት በሚገባ የፈተሻ ሰነድ ለኣመራሩ ቀርቦ ሰፊ ውይይትና ክርክር ተደርጎበታል፡፡
በዚህ መድረክ በቀረበዉ ሰነድ ላይ ተመስርቶ በተደረገ ጥልቅ ዉይይት የህዝባችንና የመላው አባላችንን ተደጋጋሚ ጥያቄ ለመመለስ ያልተቻለው በዋናነት ስትራቴጂክ አመራሩ ከገባበት አዙሪት ውስጥ መውጣት አቅቶት ሲዳክር በመቆየቱ መሆኑን የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ አረጋግጧል፡፡
አመራሩ የሃሳብና የተግባር አንድነት የጎደለው፣ ፀረ ዴሞክራቴክ ተግባርና አስተሳሰብ ውስጥ በስፋት የተነከረ፣ በተልዕኮ ዙርያ በመተጋገልና በመርህ ላይ የተመሰረተ አመራር የማይሰጥ፣ ህዝብንና አላማን ከማስቀደም ይልቅ የራሱን ክብርንና ጥቅም የሚያስቀድም መሆኑ ታይቷል፡፡ ለህዝብ ያለው ወገንተኝነት እየተሸረሸረ፣ ከኣገልጋይነት ይልቅ ራሱን እንደ ተገልጋይ እየቆጠረ፤ መዋቅራዊ ለውጥ በሚያመጡ ስኬታማ የህዝብ ዙርያ መለስ እንቅስቃሴ ከመጠመድ ይልቅ በተደማሪ ለውጦች የሚረካና በውሸት ሪፖርት ራሱን መሸለም የሚቃጣው አመራር እየሆነ በአጠቃላይ ራሱን ወደ ጥገኛ ገዢ መደብ የመሸጋገር አዝማሚያ የተጠናወተው መሆኑን በትክክል አስፈቀምጧል፡፡
ይህ የስትራተጂካዊ አመራር ድክመት በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግቦቻችን አፈፃፀም ላይ እጅግ ከባድ ተፅእኖዎች ፈጥረዋል፡፡ በህዝብ ዙርያ መለስ ተሳትፎና በጠራ መስመር ማስመዝገብ የጀመርናቸውን በርካታ ለውጦች ማስቀጠል ያልተቻለበት አንዳንዴም ወደሃላ መመለስ የጀመሩበት ሁኔታ እንደነበረ በጥልቀት ታይታል፡፡ ሁሉንም የልማት ሃይሎች በተደራጀ መልኩ በመምራት ረገድ የነበረውን ሰፊ ክፍተትንም ኣይቷል፡፡ ወጣቶች ፣ ምሁራን፣ ሴቶችና ሌሎችም የሞያ የማሕበራትና መሰል ኣደረጃጀቶች የለውጥ ባለቤት ሆነው የሚውጡበትን ዕድል በማምከን ድርጅቱን በቀጣይነት የሚመራ ብቁ ሃይል እንዳይፈጠር እንቅፋት የሆነ ኣመራር መሆኑንም በሚገባ ተረድቷል፡፡ ህዝቡ በድርጅቱ ላይ የነበረዉን እምነት እንዲሸረሸርም ትልቅ አስተዋፅኦ ኣድርጓል፡፡
በአመራሩ ዘንድ የታየው ድክመት በህዝብ ዘንድ ካስከተለው ከፍተኛ የአመኔታ መሸርሸር ችግር በተጨማሪ በከተማም በገጠርም በጀመርናቸው ትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ሰራዎቻችን ለአደጋ ያጋለጠ እንደነበረ ማእከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ በገጠርም በከተማም የቀረፅናቸው ፖሊስዎችና የቀየስናቸው ስትራተጅዎች ትክክለኝነት ላይ የሚያጠራጥር ነገር ባይኖርም ኣፈፃፀማችን የደረሰበት ደረጃ ባቀድነው ልክ ኣስተማማኝ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ በህዝባችን ዘንድ ተገቢ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ማድረጉም በትክክል ለይቷል፡፡ በገጠር የእርሻ ትራንስፎርሜሽን፣ በከተማ የኣነስተኛና ጥቃቅን ልማት፣ የከተሞች እድገት፣ የወጣቶች እና ሴቶች ስራ ፈጠራ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕድገት ባቀድነዉ ልክ ላለመመዝገቡ የስትራተጂክ አመራሩ ድክመት ዋናውን ድርሻ እንደሚወስድ ገምግሟል፡፡
የችግሩን ጥልቀትና የኣመራሩን ሁኔታ በስፋት ከገመገመ በኃላ ማእከላይ ኮሚቴው ለተፈጠረው የአመራር ችግር ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት በማመን ቀጥሎ ያከናወነው በመላው የማእከላይ ኮሚቴው ኣባላት የሚደረግ የሰላ ሂስና ግለሂስ ነው፡፡ ለተፈጠረው ችግር ማእከላዊ ኮሚቴው በኣጠቃላይ ተጠያቂ ቢሆንም የችግሩ የከፋ መገለጫ የህወሓት ስራ ኣስፈፃሚ ኮሚቴ እንደ ኣካልም ሆነ እንደ ግለሰብ ኣመራሩ መሆኑን በመውሰድ ጥልቅ የሂስና ግለ ሂስ መድረክ ኣካናውኗል፡፡ የሂስና ግለሂስ መድረኩ አላማ በግለሰብ ኣመራር አባላት ላይ ያተኮረ ሳይሆን ድርጅቱ ካለዉ ስትራተጂካዊ ፖለቲካዊ ተልእኮ አንፃር እያንዳንዱ አመራር ሃላፊነቱን የተወጣበትን ደረጃ እና ልክ በትክክል ለመገንዘብ እና አስፈላጊዉን የእርምት እርምጃ ለመዉሰድ ያለመ ነበር፡፡ ሂደቱም በግልፅነት ፣ በሙሉ ተሳትፎና በቁጭት መንፈስ የተከናወነ ሲሆን በመጨረሻም መላዉ አመራር ዘንድ በተደረሰበት ድምዳሜ ዙርያ የጋራ መግባባት የተያዘበት ሁኔታ ተፈጥራል፡፡
ማእከላይ ኮሚቴዉ የሂስና ግለሂስ ሂደቱን ካከናወነ በኃላ በድርጅቱ ስትራቴጂክ አመራር ዘንድ በስፋት ይስተዋል የነበረዉን የሃሳብና የተግባር አንድነት ችግር ስር ነቀል በሆነ መልኩ ለመፍታት የሚያስችል መግባባት ላይ የተደረሰበት የአመራር ሽግሽግ በማድረግ የተሃድሶው ስትራቴጂክ አመራር ተጠናክሮ የወጣበት የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥሯል ፡፡
የተከበራችሁ የድርጅታችን አባላት፣ አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎች
ህወሓት የትግራይ ህዝብ የትግል ውጤት እና መሪ ድርጅት ነው፡፡ ጥንካረው ለህዝቡ ካለው ታማኝነትና ወገንተኝነት የሚመነጭ ነው፡፡ ህወሓት ፈተናዎች ባጋጠሙት ቁጥር ከህዝብና አባላቱ ጋር በመሆን ችግሩን እየፈታ ለበርካታ አስርት ዓመታ ዘልቋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ጥያቄዎችህን በመፍታት ረገድ የህወሓት አመራር ከፍተኛ ድክመት አሳይቶም ጭምር በትዕግስት እና በተስፋ መጠበቃችሁ ድርጅቱ ይገነዘባል፡፡ ማእከላይ ኮሚቴው ችግሩን በሚገባ ተረድቶ የናንተን ጥያቄዎችንና ፍላጎቶች ለመፍታት፣ በህዝብ ዘንድ በብዙ መልኩ ተሸርሽሮ የነበረውን አመኔታ ለማሳደስ የሚተጋ፣ በሃገር ኣቀፍ ደረጃ ሊኖረን የሚገባውን ገንቢ ሚና ለማስቀጠል ዝግጅነቱ ፣ ተኣማኒነቱና ፅናቱ ያለው፤ ስኬቶቻችንን ለማስቀጠል የቆረጠና ቀጣዩን ጉባኤ ኣሳታፊ በሆነ መልኩ ለማከናወን የሚያስችል ስራዎችን የሚሰራ ኣመራር እንደሚሆን ኣንጠራጠርም፡፡ አመራሩ በጊዜ የለም መንፈስ ከመላው አበላችንና ህዝባችን ጋር በሚደርገው ጥልቅ ውይይት ያስቀመጣቸው ኣቅጣጫዎች በበለጠ ለማበልፀግ የሚያስችል ስራ የሚሰራ ይሆናል፡፡
የጉባኤ ዝግጅታችን መላው አባላችን፣ ምሁራን፣ ወጣቶች ፣ ሴቶችና ቡዙሃን ማሕበራትን በነፃነት ባሳተፈ መልኩ እንዲካሄድና በተመረጡ የህዝብ አጀንዳዎች ላይ አተኩሮ ለማካሄድ የሚያስችል ዙርያ መለሽ ዝግጅት የሚደረግ ይሆናል፡፡ እንደተለመደው ሁሉ አሁንም ከጎናችን ቁማቹህ ለጥቅማቹህ መረጋጥ እንድትታገሉ ድርጅታቹ ህወሓት ጥሪውን ያቀርባል ፡፡
የተከበራችሁ የክልላችን ምሁራንና ልማታዊ ባለሃብቶች
የህወሓት/ ኢህአዴግ አመራር በሚፈለገው ደረጃ የተመቻቸ ሁኔታ ባለመፈጠሩ ምክንያት በክልላችሁና በሃገራችሁ ጉዳይ ላይ በሚገባው ደረጃ ያላሳተፍናችሁ መሆኑን ተገንዝቧል በመሆኑም ጥያቄያችሁን ለመመለስ የራሳችሁን የተሟላ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ህወሓት/ኢህአዴግ ምሁሩና ባለሃብቱ በመሰላችሁ አደረጃጀት ውስጥ ሁናችሁ ተዋናይ የምትሆንበት ተቋማዊ መሰረት በማስቀመጥ ከልቡ የሚሰራ ይሆናል፡፡ በጥናትና ምርምርም ሆነ በልማት የክልላችንም ሆነ የሃገራችን ልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ባለቤት የምትሆኑበት ሁኔታ ይመቻቻል ፡፡
የተከበራችሁ የክልላችን ወጣቶችና ሴቶች
በክልላችን ልማትም ሆነ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላችሁ ተሳትፎ ለሃገራችን ዕድገትና ህዳሴ መረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡ ከምንም በላይ የተጠቃሚነትና የተሳታፊነት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚንቀሳቀስ ድርጅታችሁ ህወሓት/ኢህአዴግ ቃል ይገባል ፤ እናንተን በፅሞና ለማዳመጥና ለማታገል የሚያስችሉ መድረኮችንም ያመቻቻል ፡፡
ዉድ የኢህአዴግ እህትና አጋር ድርጅቶች
በልማትና በመልካም አስተዳደር ዙርያ ህዝባችን ለከፍተኛ ምሬት የዳረጉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በኣመራሩ ድክመት የተፈጠሩ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጅታችን ህወሓት/ ኢህአዴግ በአገር ደረጃ በሚደረጉ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎቻችን በማሳካት ረገድ ሲጫወት በመጣው ሚና ላይ ኣሉታዊ ተፅእኖ መፍጠሩንም በሚገነባ ይገነዘባል፡፡ የኣመራር ድክመት በህወሓት ውስጥም ሆነ በክልላችን በሚደረጉ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጥረቶች ላይ ጉዳት ከማድረሱ በተጨማሪ በእህትና በአጋር ድርጅቶች መካከል ለበርካታ ኣስርት ኣመታት የነበረውን በመርህ እና በትግል ላይ የተመሰረተ ውህደት፣ ለዙርያ መለሽ ስኬት ያበቃን የአመለካከትና የተግባር ኣንድነት በየጊዜው እየተሸረሸረ እንዲመጣና በጋራ ዓለማ ዙርያ በአንድ ልብና መንፈስ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በንትርክና በጥርጣሬ መተያየት ያጠላበት እንዲሆን በማድረግ በኩል የራሱን ኣሉታዊ ኣስተዋፅኦ እንደደረገ በትክክል ኣስቀምጣል፡፡
ሁሉንም አቅሞቻችን፣ የህዝባችንን ፍትሓዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ የጠሩ ፖሊሲዎቻችን ሲኬታማ ኣፈፃፀም ላይ ከማድረግ ይልቅ የፌዴራል ስርዓት ጠላቶች ባጠመዱልን ወጥመድ ውስጥ ገብተን የሃገራችንን ኢትዮጵያ ህልውና ፈተና ላይ እንዲወድቅ በማድረግ ረገድ በህወሓት ኣመራር ዘንድ የታየው ድክመት የማይናቅ ሚና እንደነበረው በግልፅ ይረዳል፡፡ የፈዴራል ስርዓቱን ለመናድ ከውስጥም ከውጭም የተሰባሰቡ ጥገኛ ሃይሎችን በጋራ የመመከት ኣቅማችን እየተመናመነ በተመሳሳይ ፕሮግራምና ልማታዊ መስመር ዙርያ የተሰለፉ ሃይሎች የጋራ ትግላቸዉ መደነቃቀፍ የጀመረበት ሁኔታ ተፈጥራል፡፡ በኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች ውስጥ ለሚታዩ ችግሮች ዋነኛው ተጠያቂነት ለየድርጅቱ ኣመራር የሚተው ቢሆንም በህወሓት ኣመራር ውስጥ ይታዩ የነበሩ ኣዝማሚያዎች ለብዙ ኣስርተ ዓመታት በእሳት ጭምር ተፈትኖ የመጣውንና ለሃገራችን ኢትዮጵያ ልማትና ዴሞክራሲ እውን መሆን ምክንያት የሆነው አብዬታዊና ዲሞክራሲያዊ አንድነት በመሸርሸር ረገድ የማይናቅ ድርሻ እንዳነበረው ማእከላዊ ኮሚቴው ባደረገው ግምግማ ኣረጋግጧል፡፡
ህወሓት ከእህት እና አጋር ድርጅቶች ያለውን ግንኝነት በመርህና በመተጋገል ላይ በመመስረት የሚታደስበት የነበሩ የርስ በርስ መጠራጠሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ኣቅጣጫዎችን የሚከተል ይሆናል፡፡
ዉድ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች፣ ላብአደሮች፣ ልማታዊ ባለሃብቶች
ህወሓትና የትግራይ ህዘብ ከሌሎች እህትና ኣጋር ድርጅቶች እንዲሁም ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን ለእኩልነትና ለፍትሓዊ ተጠቃሚነት የከፈሉት እጅግ ከፍተኛ መስዋዕትነት ሳይበቃውና ተከታታይ ገዢዎች ያሲረፉበት ቁስል በወጉ ሳያገግም ለሌላ የተቀናጀ ጥቃት የሚጋለጥበት ሁኔታ ከመፍጠር ኣንፃር የህወሓት ኣመራር ውስጥ የታየው ድክመት የማይናቅ ኣስተዋፅኦ ኣድርጓል፡፡
አሁንም ቢሆን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ያመጣቸዉን ትሩፋቶች ጠብቆ የተሻለ ብልፅግና የሰፈነባት እና ህዳሴዋ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን እዉን ለማድረግ በሚደረገዉ እንቅስቃሴ ዉስጥ ድርሻዉን ኣጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ከዉጭም ከዉስጥም የሚቃጡብንን አፍራሽ ጥቃቶች ለመመከት ከመላዉ የሃገራችን ህዝቦች ጋር በቅርበት ይሰራል፡፡ በአሁኑ ሰአት በየአካባቢዉ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትና የህዝቦች የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የልማት ጥያቄ በተገቢዉ መንገድ ለመመለስ በሚደረገዉ ርብርብ ዉስጥ ድርሻዉን ለማበርከት ዝግጅነቱን ይገልፃል፡፡ ህወሓት/ኢህኣዴግ የጋራ ሃገራችንን በሆነችው ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለልማትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የተጫወተውን ገንቢ ሚና ኣጠናክሮ ለመወጣት የሚያስችለውን ኣቅጣጫዎች ከህዝቦች ጋር በመመካከር የሚያከናውን ይሆናል፡፡ ዲሞክራሲያዊ አንድነታችሁን አጠናክራችሁ አፍራሽ አጀንዳዎቻችውን ለማሳካት ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚዳክሩ ጠላቶችን በጋራ እንድንመክት ጥሪውን ያቀርባል ፡፡
የህወሓት ማ/ኮሚቴ
ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማእታት
ህዳር 21/2010 ዓ.ም