አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከአሜሪካ ሴኔትና ኮንግረስ አባላት ጋር በሠላምና ጸጥታ ማስከበር ጉዳዮች ላይ ተወያዩ።
የኢትዮጵያና የአሜሪካን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ከኮንግረሱም ሆነ ከሴኔቱ ምክር ቤቶች ጋር ያለው ግንኙነት እንደሚጠናከር ተገልጿል።
በውይይቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የክልል ፕሬዚዳንቶችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንደገለጹት ኢትዮጵያና አሜሪካ በውጭ ግንኙነት መርህ መሠረት በርካታ ስራዎችን በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ።
ከጸጥታ ጋር ተያይዞ በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለውን ዓለም ዓቀፍ ሽብርተኝነት ለመዋጋት በጋራ መስራታቸውን መጥቀስ ይቻላል ብለዋል።
ለሴኔቱ አባላትም እነዚህ ስራዎች ወደፊትም ይበልጥ ተጠናከረው እንዲቀጥሉ ኢትዮጵያ አሁን እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተገልጾላቸዋል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ሴናተሮቹ ኢትዮጵያን በደንብ የሚያውቁ፣ የሚወዱና የኢትዮጵያ ህዝቦችን ሁኔታ ጠንቅቀው የተረዱ በመሆናቸው ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክረዋል ብለዋል።
የሴኔቱ አባላት ተወካይ ሴናተር ጀምስ ኢንሆፍ በበኩላቸው ላለፉት 23 ዓመታት የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሁኔታ ሲከታተሉ መቆየታቸውንና የአገሪቷ ወዳጅ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሴናተር ጀምስ ኢትዮጵያ ውስጥ አስደናቂ ለውጦች መምጣታቸውን መታዛባቸውን ተናግረው አሜሪካም ጥሩ አጋሯ ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር በተሻለ መልኩ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች መምጣቷን መገንዘባቸውንም አክለዋል።
ኢትዮጵያና አሜሪካ ከሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ባሻገር በቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ሽብርተኝነትን በመዋጋት ትብብራቸው ይታወቃሉ።