አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 13 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃለይ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተወያዩ።
ኢትዮጵያ በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ሰላምና ፀጥታ ላይ የምታደርገው ጥረትም የውይይታቸው አካል ነበር ተብሏል።
ከዚህ ባለፈም የምስራቅ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድን) ማጠናከር በሚቻልበት አግባብ ላይም መክረዋል።
አምባሳደር ኒኪ ኢትዮጵያ በቀጠናው በተለይም በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ሰላምን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረትም አድንቀዋል።
አምባሳደሯ ከአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሚናታ ሰማቴ ጋርም፥ በደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት እና በፀረ አልሸባብ ትግሉ ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ወቅትም ሃገራቸው በሶማሊያ የአልሻባብ የሽብር ቡድንን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት፥ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህብረት በግጭት ውስጥ የሚገኙ የደቡብ ሱዳን አካላትን ወደ ሰላም ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት ያደነቁት አምባሳደር ኒኪ፥ በሃገሪቱ ያለውን ቀውስ ለመፍታት ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ መፍትሄ ያሻል ብለዋል።
ለዚህም ኢጋድ እና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች አካላት ተመሳሳይና የጋራ አቋም በመያዝ አፍሪካዊ መፍትሄ ሊያመጡ ይገባልም ነው ያሉት።
በአህጉሪቱ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ወጣት በመጠቀም ለውጥ ማምጣት ይቻላል ያሉት አምባሳደር ኒኪ፥ ይህን ሃይል በፀረ ሽብር ትግሉ መጠቀም እንደሚገባም አንስተዋል።
የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሚናታ ሰማቴ በበኩላቸው፥ በምስራቅ አፍሪካ ለሚካሄደው ፀረ ሽብር ዘመቻ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ኮሚሽነሯ የአፍሪካ ሀብረት ለሚያካሂደው ዘመቻ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አምባሳደር ኒኪ የኢትዮጵያ ቆይታቸውን ሲያጠናቅቁ በደቡብ ሱዳንና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ጉብኝት ያደርጋሉ።