Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የአምባሳደሮችና የሚሲዮን ሀላፊዎች ስብሰባ በሀዋሳ እየተካሄደ ነው


አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 29፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአምባሳደሮችና የሚሲዮን ሃላፊዎች ስብሰባ በሀዋሳ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ስብሰባው “ተቋማዊ ለውጥ ለውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ስኬት” በሚል መሪ ቃል ነው በመካሄድ ላይ የሚገኘው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፥ ኢትዮጵያን በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን መድረኮች ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበርና ተደማጭነቷን ለማጉላት የተከናወኑት ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩና ለቀጣይ ስራዎች ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረው ያለፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ሰራተኞች አስተዳደር እና የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ማቋቋሚያ ደንቦች በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲጸድቁ ተደርጓልም ብለዋል።

በዲፖሎማሲያዊ ግንኙነት ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ባጀት ዓመት በሠላምና ፀጥታ ረገድ ባደረገችው እንቅስቃሴ በክልላዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ከመሰል አገሮች ጋር በመተባበር በመርህ ላይ በመመስራት ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር መቻሉ ዶክተር ወርቅነህ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ወራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነቷ የነበራት ተሳትፎ ውጤታማና ተደማጭነቷን ከፍ ያደረገ እንደነበርም ዶክተር ወርቅነህ ተናግረዋል።

የኢኮኖሚ ትብብር እና አጋርነትን ለማጠናከርና የዳያስፖራ ሚና ለማሳደግ የተሰሩት ስራዎች አበረታች እንደነበሩም ገልፀዋል።

ስብሰባው እስከ ጳጉሜ 03 ቀን 2009 ዓ.ም የሚቀጥል ሲሆን፥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች ያከናወናቸውን ተግባራት የሚገመገም ይሆናል።

ከሃዋሳ ዮኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴ ዙሪያ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አምባሳደሮቹና የሚሲዮን ሃላፊዎቹ ነሃሴ 25 እና 27 2009 ዓ.ም ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር የስራ ክንውናቸውን በአዲስ አበባ መገምገማቸው ይታወሳል።