Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የግብርና መር ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቀጣይነት ያለው ውጤት ለማስመዝገብ ትልቅ ድርሻ አለው ተባለ


አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 15፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የቀየሱት የግብርና መር ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቀጣይነት ያለው ውጤት በማስመዝገብ በኩል ትልቅ ድርሻ አለው ተባለ።

የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ 5ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተካሄደባቸው ይገኛል።

በውይይቱ ላይ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ምሁራን ተገኝተዋል።

በፓናል ውይይቱ ሁለት ኢኮኖሚ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን፥ በታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የተነደፉት ግብርና ላይ ያተኮሩ የኢኮኖሚ እድገት ከሌሎች ሀገራት ጋር ተነጻጽሮ ቀርቧል።

ታላቁ መሪ መለስ በህይወት እያሉ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም የታችኛውን መደብ ማዕከል ያደረገ በትንሽ እርሻ ላይ የተመሰረተ የግብርና ስትራቴጂ በመንደፍ ተግባራዊ አድርገው ነበር ተብሏል።

በዚህም ከ20 ዓመት በፊት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ይገኝ የነበረውን 10 ኩንታል ምርት አሁን ላይ ወደ 22 ከፍ ማድረግ ተችሏል ነው የተባለው።

ይህም አርሶ አደሩ የሚያገኘው ምርት በእጥፍ ያደገበት እና ከእለት ጉርሱ አልፎ ለገበያ በማቅረብ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያድግ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑም በመድረኩ ላይ ተነስቷል።

የግብርና መር ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ሀገሪቱ እድገት እንድታስመዘግብ እና አሁን ላይ እያደረገች ወዳለው ወደ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ሽግግር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ተገልጿል።

እነዚህም የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ውጤት መሆናቸውን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ንዋይ ገብረአብ ተናግረዋል።

ውይይቱ አሁንም ቀጥሎ በመካሄድ ላይ ሲሆን፥ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተካሄደባቸው ይገኛል።

የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የአምሰተኛ ዓመት መታሰቢያ “‘የሃሳብ ድህነትን ታግሎ ያሸነፈ መሪ’ በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል።

በትናንትናው እለትም የታላቁ መሪ 5ኛ ዓመት መታሰቢያ በችግኝ ተከላና በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ተዘከሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የትግል አጋሮች በጉለሌ እፅዋት ማዕከል በመገኘት ችግኝ ተክለዋል።

የችግኝ ተከላው ታላቁ መሪ መለስ ለአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ የነበራቸውን ታላቅ ራዕይ ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተነግሯል።

የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ 5ኛ ዓመት መታሰቢያ በአዲስ አበባ ኤግዚቪሽን ማእከል የተዘጋጀ የፎቶ አውደ ርዕይን ፕሬዚዳንት ሙላቱ በትናንትናው እለት ከፍተውታል።

አውደ ርዕዩ እስከ ፊታችን አርብ ነሃሴ 19 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ለጎብኝዎች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ነው የተገለጸው።