Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

እራሱን ቤህነን ብሎ የሚጠራው ቡድን መመለስ በክልሉ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት ውጤት ነው— አቶ አሻድሊ ሃሰን


አሶሰሳ ሀምሌ 4/2009 ራሱን የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን) ብሎ የሚጠራው ቡድን አባላትና አመራሮች መመለሳቸው በክልሉ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት ክልሉ ያለው የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሁኔታ ፣ እየተመዘገበ የሚገኘው የልማትና የመልካም አስተዳደር ስኬት የቡድኑ አባላትና አመራሮች ወደ ክልሉ እንዲመለሱ ምክንያት ሆኗል፡፡

ሀገሪቱ ሰላምን መሰረት አድርጋ መስራቷ ተከታታይና ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ድህነትን በአጭር ጊዜ ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

“የክልሉ ህዝቦችም የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ቀጣይነት ሊኖረው የሚችለው ሠላም ሲረጋገጥ እንደሆነ በመገንዘብ ፀረ ሰላም ኃይሎችን በመታገል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ “ብለዋል፡፡

ህዝቡ ለሰላሙ መጠበቅ ያለው ቁርጠኝነት የቡድኑ አባላትና አመራሮች ወደ ክልላቸው በመመለስ በሠላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስገድድ መሆኑን አቶ አሻድሊ አስታውቀዋል፡፡

የውጭና የውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎች ኤርትራን የመሳሰሉ አገራትን ማዕከል በማድረግ ሰላምና ልማትን ለማደናቀፍ ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል፡፡

የቡድኑ አባላትና አመራሮች ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ በተደረገው ጥረት ውስጥ ድርሻ ለነበራቸው አካላት ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

“ለተመለሱት የቡድኑ አባላት በሕገ-መንግስቱ ዙሪያ ስልጠና እንደሚሰጣቸውና በተለያዩ የሥራ መስኮች በመሰማራት የራሳቸው መተዳደሪያ እንዲኖራቸው ክልሉ እገዛ ያደርጋልም” ብለዋል፡፡

እራሱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ነጻነት ንቅናቄ ብሎ የሚጠራው ቡድን 95 አባላት የአመጽ ድርጊታቸውን ትተው ከመንግስት ጋር በመስማማት በቅርቡ ወደ ሀገራቸው መግባታቸውንና ከመካከላቸውም 15ቱ በካርቱም ይኖሩ የነበሩ የድርጅቱ አመራር አካላት እንደሆኑ ተመልክቷል፡፡