Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለስራ ጉብኝት ወደ እስራኤል አቀኑ


አዲስ አበባ ግንቦት 27/2009 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለስራ ጉብኝት ዛሬ ወደ እስራኤል አቀኑ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ እስራኤል ያቀኑት የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባደረጉላቸው ግብዣ ነው።

እስራኤል በሳይንስና ቴክኖሎጂ አንዲሁም በዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎቿ ትታወቃለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተመራው የልዑካን ቡድንም አገሪቷ በእነዚህ የቴክኖሎጂ መስኮች እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራትን ይጎበኛሉ።

ኢትዮጵያ በተለይም በዘመናዊ ግብርና፣ በውሃና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ከእስራኤል ልምድ መቅሰም ትሻለች።

በስራ ጉብኝቱ በኢትዮጵያና እስራኤል መካከል የሁለትዮሽ ውይይቶች የሚካሄዱ ሲሆን የተለያዩ ስምምነቶች እንደሚፈረሙም ይጠበቃል።

ባለፈው ዓመት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በባሕልና ቱሪዝም መስኮች በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያና እስራኤል ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከ60 ዓመታት በፊት የተጀመረ ይሁን እንጂ ግንኙነታቸው ከሶስት ሺህ ዓመታት በፊት ነበር የተጀመረው።

የሁለቱ አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጠንካራ ቢሆንም ግንኙነቱ በንግድና ኢንቨስትመንት መታገዝ ከጀመረ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የሚሄድ አይደለም።

የእስራኤል ኩባንያዎች ባለፉት 15 ዓመታት በኢትዮጵያ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተሳትፈዋል።