Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የመጀመሪያው “የቻይና የንግድ ሣምንት በኢትዮጵያ” በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው


አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመጀመሪያው “የቻይና የንግድ ሣምንት በኢትዮጵያ” ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።

ከሰኔ 27 እስከ 29 ቀን 2009 ዓ.ም በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል የሚካሄደው አውደ ርዕይ አዘጋጆች መቀመጫውን ዱባይ ያደረገው የቻይናው ኤም አይ ኢ ኢቨንትስ እና አገር በቀሉ ፕራና ፕሮሞሽን ናቸው።

የኤም አይ ኢ ኢቨንትስ ዳይሬክተር ሜሼል ማይሪክ፥ ዓውደ ርዕዩ የኢትዮጵያና ቻይና ኩባንያዎችን የንግድ ልውውጥና ትስስር እንደሚያሳልጠው ገልፀዋል።

ከቻይና ኩባንያዎች ጋር የንግድ ልውውጥ ያልነበራቸው ኢትዮጵያውያንም በቀላሉ መገበያየት የሚችሉበትን እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

አውደ ርዕዩ “ቻይና ወደ አፍሪካ የምትልካቸው ምርቶች ብዛት እንጂ ጥራት የላቸውም” ስለሚባለው የተሳሳተ ግንዛቤ ትክክለኛ መረጃ የሚገኝበት እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ተሳታፊዎቹ ኩባንያዎች በኢነርጂ፣ በቤት ውስጥ መገልገያ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች፣ በግንባታ እቃዎች፣ ማሽነሪዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ስማርት ኤሌክትሮኒክስ ምርቶች፣ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው።

የጤናና ውበት መጠበቂያ ምርቶች፣ የቤት ውስጥ ማስዋቢያና የሆቴል እቃዎች፣ የህትመት ፓኬጂንግና ፕላስቲክ፣ የጎማና ተሽከርካሪ አካላት፣ የእርሻ መሳሪያዎች፣ የምግብና መጠጥ ቴክኖሎጂና የእንስሳት ህክምና ምርቶችም በአውደ ርዕዩ ለሽያጭ ይቀርባሉ።

የኢትዮጵያ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ልማት ኢንስቲትዩት የገበያና ፕሮሞሽን ባለሙያ አቶ ሃብታሙ ይስሃቅ፥ ዓውደ ርዕዩ አገሪቱ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የምታደርገውን እንቅስቃሴ ለማሳካት ልምድ ታገኝበታለች ብለዋል።

ለቻይና ባለሃብቶችም በአገሪቱ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት የገበያ አማራጮችን የሚያዩበት እድል እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ እንደሚያሳየው የሁለቱ አገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መደበኛ በሆነ መንገድ መካሄድ የጀመረው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1972 ኤምባሲያቸውን በከፈቱበት ወቅት ነው።