Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም በተመለከተ የተለቀቀውን ረቂቅ አዋጅ መንግሥት አላውቀውም አለ


‹‹በፌዴራል ደረጃ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ያለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው››

የኦሮሚያ ክልል

‹‹የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ›› በሚል ርዕስ የተለቀቀውን ረቂቅ ሰነድ፣ መንግሥት እንደማያውቀው አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ረቂቅ አዋጆች የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓትን ተከትለው የሚያልፉ እንጂ ለማኅበራዊ ድረ ገጽ ፍጆታ የሚውሉ አይደሉም፡፡

‹‹እኛ የምናውቀው ሰነድ አይደለም፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ በመንግሥት በማይታወቅ ሰነድ ላይ ማብራሪያ መስጠት እንደሚቸገሩም ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተለቀቀውን ረቂቅ የሕግ ሰነድ ያውቀው እንደሆነ የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹በፌዴራል ደረጃ የሚተገበር ሕግን የማርቀቅ ኃላፊነት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን የኦሮሚያ ክልል በፌዴራል ደረጃ የሚወጣው ሕግ ሊያካትታቸው ይገባቸዋል ያላቸውን ጉዳዮች ለፌዴራል መንግሥት ማስታወቁን ጠቁመዋል፡፡

‹‹የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ›› ተብሎ የተለቀቀው የሕግ ረቂቅ ሰነድ የአዲስ አበባ ከተማ ስም በጽሑፍ ‹‹ፊንፊኔ/አዲስ አበባ›› ተብሎ መጠራት እንዳለበት ይገልጻል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ኦፊሴላዊ ቋንቋ አማርኛና አፋን ኦሮሞ እንዲሆን የሚል አንቀጽ ይዟል፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 ሥር ከንዑስ አንቀጽ አንድ እስከ አምስት ድረስ ስለአዲስ አበባ የተደነገገ ነው፡፡

በድንጋጌዎቹ መሠረት አዲስ አበባ የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግሥት ስለመሆኑና ከኦሮሚያ ክልል ጋር ስላለው የጥቅም ግንኙነት ይገልጻል፡፡

ይህንን የጥቅም ግንኙነት የሚገልጸው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ አምስት ሲሆን፣ ‹‹የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፤›› ይላል፡፡

በማኅበራዊ ድረ ገጾች የተለቀቀው ረቂቅ የተባለው ሰነድ ይህንኑ ጥቅም ለማስጠበቅ የተረቀቀ ቢሆንም፣ ከላይ የተጠቀሰው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ እንደማይገድበው ይገልጻል፡፡

‹‹በዚህ (ረቂቅ) አዋጅ ውስጥ የተጠቀሱት ዝርዝር የክልሉ መብቶችና ልዩ ጥቅሞች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ (5) ላይ የተገለጸው አጠቃላይ አነጋገር የሚገድበው አይሆንም፤›› በማለትም ይገልጻል፡፡

ይህ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቀ ረቂቅ ሰነድ በ14 ገጽ የቀረበና 46 ገጽ አባሪ ማብራሪያዎችን የያዘ ነው፡፡