አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን እስከ 16 ዓመት በባለሀብቶች ተይዞ ሳይለማ የነበረ 300 ሄክታር የሚጠጋ መሬት ለወጣቶች እንዲሰጥ ተደርጎ ወደ ስራ ገብቷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በምስራቅ ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ለወጣቶች መሬት ተላልፎ ተሰጥቷል።
በዚህም አደአ ወረዳ በቆፍቱ ቀበሌ በኢንቨስትመንት ስም የተያዘ እና በህገ ወጥ መንገድ ጥቅም ላይ ሲውል የነበረ ከ73 ሄክታር በላይ መሬት ለወጣቶች ተላልፎ ተሰጥቷል።
መሬቱን ፌሪ ፊልድ የተባለ ኩባንያ በ1993 የተቀናጀ የግብርና ስራን ዘመናዊ በሆነ መንገድ እና የአካባቢው አርሶ አደሮች ከሚሰሩት እርሻ በተለየ መልኩ ለማከናወን በሚል ነበር የወሰደው።
ሆኖም ግን መሬቱ ላይ ጥበቃ በመቅጠር የአካባቢው አርሶ አደር ከሚያመርተው ባነሰ መልኩ መልኩ ምንም አይነት ቴክኖሎጂ ሳይጠቀም ጤፍ፣ ስንዴ እና ሽንብራ ሲያመርት ነበር ተብሏል።
መሬቱን በኢንቨስትመንት ስም የወሰዱት ባለሀብትም በውላቸው መሰረት መሬቱን እያለሙ አለመሆኑን የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በጥናት ካረጋገጠ በኋላ ውላቸው እንዲቋረጥ በማድረግ መሬቱ በ16 ማህበራት ለተደራጁ ከ400 በላይ ወጣቶች ተላልፎ እንዲሰጥ አድርጓል።
እንዲሁም ወጣቶቹ መሬቱን ዘመናዊ በሆነ መልኩ እንዲያለሙም አራት የእርሻ ትራክተሮች ከክልሉ መንግስት ተበርክቶላቸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በዛሬው እለት ለወጣቶቹ የመሬቱን ሳይት ፕላን እና የትራክተሮቹን ቁልፍ አስረክበዋል።
መሬቱን የተረከቡ ወጣቶች እውቀታቸውን እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለራሳቸው ተጠቅመው ሀገርንም እንዲጠቅሙ ርእስ መስተዳድሩ መልእክት አስተላልፈዋል።
በተያያዘ በምስራቅ ሸዋ ዞን ወንጂ አካባቢ በማህበር ተደራጅተው በከብት ማደለብ ለተሰማሩ 800 ወጣቶች በዛሬው እለት መሬት ተሰጥቷቸዋል።
ለወጣቶቹ ተላልፎ የተሰጠው መሬትም በከብት ማደለብ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው መሬት ከተረከቡ በኋላ ወድ ስራ ካልገቡ ባለሀብቶች ተወስዶ የተሰጠ መሆኑም ተገልጿል።
በከብት ማደለብ ስራ ለተሰማሩ ወጣቶች የገበያ ትስስርን ለመፍጠር የሚያስችል እና ስጋን ወደ ውጭ ሀገር ለመላክ የሚያስችል የቄራ ግንባታ መሰረተ ድንጋይም በሉሜ ወረዳ በክልሉ ርእሰ መስተዳድት አቶ ለማ መገርሳ አማካኝነት ተቀምጧል።
በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳን የተመራው ልኡክም በምስራቅ ሸዋ ዞን ለወጣቶች የተፈጠሩ የስራ ዕድሎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በሀይለኢየሱስ ስዩም