Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሹምሽር አደረጉ

የቀድሞ የጄኔራል ኤሌክትሪክ የኢትዮጵያ ኃላፊ የቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በባህልና ቱሪዝም ሥር በሚተዳደሩ ሁለት ተቋማት አመራሮች ላይ ሹም ሽር በማድረግ፣ ሚያዝያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. አዳዲስ ተሿሚዎችን መመደባቸው ታወቀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀድሞዎቹን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰሎሞን ታደሰንና ምክትላቸውን አቶ ጀማል ከድርን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳውድ ሙሜ በአዳዲስ ተሿሚዎች መተካታቸውን ሪፖርተር ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ የአሜሪካ ጄኔራል ኤሌክትሪክ ኩባንያ ኃላፊ፣ እንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊትም የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ባልደረባ ሆነው የሠሩትን አቶ ዮሐንስ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሹመዋል፡፡ የአቶ ዮሐንስ ምክትል በመሆን የተሾሙት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር አቶ የቻለ ምሕረት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት በዚሁ ተቋም የብሔራዊ ፓርኮችና የዱር እንስሳት መጠለያዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርነት ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ናቸው፡፡

አቶ ዮሐንስ የጄኔራል ኤሌክትሪክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ለአንድ ዓመት መሥራታቸውን መረጃዎች ይቁማሉ፡፡ ለአዲሱ ሹመት እስከበቁበት ድረስ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ቺፍ የቴክሎጂ ኦፊሰር ሆነው ሲሠሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ዋናው ተጠሪነታቸው ለግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ እንደነበር ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት ለመረዳት ተችሏል፡፡ በመሆኑም በደጋፊነት ኮሚሽኑን ሲያገለግሉ እንደነበር የተገለጸላቸው አቶ ዮሐንስ፣ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ዳይሬክተር በመሆንም ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያትም በአሜሪካ ዌልስ ፋርጎ ባንክ የምርምርና ኢኖቬሽን ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንትነት የሠሩት አቶ ዮሐንስ፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፋይናንስና በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ማግኘታቸውን ከግል ማኅደራቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

አዲሱን ሹመታቸውን በማስመልከት በሪፖርተር የተጠየቁት አቶ ዮሐንስ፣ ምንም እንኳ ከ17 ዓመታት የኒውዮርክ ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለአራት ዓመታት ያህል ቢያገለግሉም፣ አዲሱ ሹመታቸውን ግን ፈጽሞ ያልጠበቁት እንደሆነና በጣም እንዳስደሰታቸው ጠቁመዋል፡፡ በመጀመርያ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በተለይ በግሉ ዘርፍ እንዲሁም በግብርናው መስክ እንዲሠሩ ተፈልጎ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ሰፊ በመሆኑና በኢንቨስትመንት መስክ በኮሚሽኑ በኩል ኢንቨስተሮችን ለመሳብ በሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ላይ መሥራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ መሀል ዓምና ወደ አሜሪካ እንዳቀኑ የገለጹት አቶ ዮሐንስ፣ በመንግሥት ጥያቄ ተመልሰው በመምጣት በቴክኖሎጂ ዘርፍ መሥራት እንደጀመሩ ያልጠበቁት ጥሪ ከመንግሥት እንደቀረበላቸው ተናግረዋል፡፡ ማክሰኞ ሚያዝያ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. የሹመት ደብዳቤያቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መቀበላቸውን የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ በመጪው ሳምንት ማክሰኞ አዲሱን ሥራቸውን በይፋ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡

የአቶ ዮሐንስ ምክትል ሆነው የተሾሙት አቶ የቻለ ምሕረት በበኩላቸው፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቱሪዝም ዘርፍ ረዳት ፕሮፌሰር ሆነው በማገልገል ላይ እንደነበሩና የተሰጣቸውን ሹመት በመቀበል ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከረዳት ፕሮፌሰርነታቸው በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ምክትል ዲን በመሆን ሲያገለግሉ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠሩት አቶ የቻለ፣ በፋሲል ግቢ የዓለም ቅርስ የአስተዳደር ዕቅድ በማውጣት ከመሳተፋቸውም በላይ፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሥር የባህል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ውስጥ ያደረጓቸው ተሳትፎዎች ከሚጠቀሱላቸው ተሞክሮዎች መካከል ይገኙበታል፡፡