Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

አዳዲስ አካሄዶች የታዩበት የብሔራዊ ኦሊምፒክ ምርጫ


አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያቀረበው ሞሽን ውድቅ ተደርጓል
በኢትዮጵያ ስፖርት ተቋማት አመራርነት ላይ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሚታየው አካሄድ መንግሥት ከእኩል በላይ ባለድርሻ በመሆን ሲሳተፍ ነበር፡፡ የመንግሥት ተቋማትን የሚመሩ ግለሰቦች ለዓመታት ተቆጣጥረዋቸው የነበሩ የስፖርት ዘርፎች ቀስ በቀስ በግል ዘርፍ ተዋንያንና ባለሀብቶች አመራርነቱን መያዝ የጀመሩበት ክስተት ተፈጥሯል፡፡

ከዚህ ቀደም በተካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች ምርጫ ወቅት ይኼው ታይቷል፡፡ በአብዛኛው በመንግሥታዊ መዋቅር ሥር የሚገኙ ተቋማትን የሚመሩ ሰዎች ይዘዋቸው የቆዩ የአመራር ቦታዎች በአትሌቶች፣ በባለሙያተኞችና በባለሀብቶች እየተተኩ ይገኛሉ፡፡ ይህ ክስተት በድጋሚ ከሰሞኑ በአዳማ ከተማ በተካሄደው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አመራር ቦርድ ምርጫ ላይ ተደግሟል፡፡ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት ሆነው መጋቢት 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዳማ ሪፍት ቫሊ ሆቴል በተካሄደው ጉባኤ ፊት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሥራ አስኪያጅ በነበሩት በአቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም ይመራ የነበረው ኦሊምፒክ ኮሚቴው፣ በአዲሱ ምርጫ በዶ/ር አሸብር ተተክተዋል፡፡ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ዶ/ር አሸብር የፓርላማ ተመራጭና በአፍሪካ የፓርላማ ጽሕፈት ቤት ኢትዮጵያን በመወከል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተከናወነው የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ብቸኛ ሆነው መቅረባቸው ይታወሳል፡፡
ለ42ኛ ጊዜ በተካሄደው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከምርጫው በፊት በአጀንዳነት የቀረቡ ጉዳዮችን ተመልክቷል፡፡ ከቀረቡት አጀንዳዎች መካከል የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የዋና ጸሐፊ ኃላፊነት ቀደም ሲል በተመራጭ የነበረው አሠራር ቀርቶ በቅጥር ሙያተኛ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ቻርተር የሴቶች የአመራርነት ድርሻ 30 በመቶ በሚለው መሠረት ሦስት ሴቶች በምርጫው ተካተዋል፡፡ የአይኦሲ አባል ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ በቀጥታ አባል ሲሆኑ ከኦሊምፒክ ስፖርቶች ውጭ ያሉትን በመወከል፣ ወ/ሮ ሔሮዳዊት ዘለቀ ከኢትዮጵያ ቦውሊንግ ፌዴሬሽንና ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ ከኦሊምፒያኖች ያለድምፅ አባል ሆነዋል፡፡ የፓርላማ አባሉ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ከፓራሊምፒክና አቶ ተስፋዬ በቀለ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርም ያለ ድምፅ በሥራ አመራር ቦርዱ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

በዕለቱ ድምፅ የመስጠት መብት ከነበራቸው 78 መራጮች ድምፅ አግኝተው ለኦሊምፒክ አመራርነት የበቁት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነት፣ ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በምክትል ፕሬዚዳንትነት፣ ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ፣ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባልነታቸው በቀጥታ፣ ዶ/ር ዳዲ ወዳጅ ከጅምናስቲክ ፌዴሬሽን፣ አቶ ኪሮስ ሀብቴ ከኢትዮጵያ ውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን፣ አቶ ዳዊት አስፋው ከወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን፣ እንዲሁም ቀደም ሲል ያለ ድምፅ የተመረጡት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ አቶ ተስፋዬ በቀለ በአባልነት ተካተዋል፡፡ ወ/ሮ ሔሮዳዊት ዘለቀ ደግሞ ዓቃቤ ነዋይ ሆነዋል፡፡

ሌላው ለጉባኤው አዲስ ነገር ሆኖ የቀረበው ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ (ሞሽን) ይጠቀሳል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለጉባኤው ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ አትሌቲክሱ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እያስመዘገበ ያለው ውጤት ግምት ውስጥ ገብቶ በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ያለ ድምፅ እንዲሰጠው የሚጠይቅ ነበር፡፡ የኦሊምፒክ ኮሚቴው የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም ጉባኤው ፌዴሬሽኑ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ (ሞሽን) ላይ እንዲወያይበት አስደርገው ጉባኤውም ፌዴሬሽኑ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ያለምንም የሐሳብ ልዩነት ውድቅ እንዲሆን ተስማምቷል፡፡ ሰብሳቢው አቶ ብርሃነ በበኩላቸው ‹‹እንዲህ ዓይነቱ የውሳኔ ሐሳብ ጥያቄ ከአንድ ትልቅ ብሔራዊ ፌዴሬሽን አይጠበቅም፡፡ የኦሊምፒክ መርህም አይደለም፤›› ብለው የጉባኤውን ውሳኔ እንደሚያስከብሩ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ጉባኤው በአብዛኛው እንደ አጀንዳ ሲያነሳው የነበረው ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የሚሰጠው ድጎማና የቁሳቁስ አቅርቦት ‹‹ያንሳል›› የሚለው ብዙውን ሰዓት የወሰደ ነበር፡፡ እነዚህ የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የዓመታት አጀንዳዎች ሆነው የዘለቁ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡

ብዙዎቹ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ብቻ እየተጠበቀ ተደጋግመው በክፍትነት ሲደመጡ የቆዩትንና አሁንም እየተደመጡ ያሉትን አጀንዳዎች አስመልክቶ አዲሱ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ያመለከቱት ነገር አለ፡፡ ለሁሉም የአገሪቱ ስፖርቶች መሠረታዊ መፍትሔ፣ ‹‹በድጎማ የቆየውን አሠራር ወደ ጎን ብሎ ስፖርቱን ወደ ገንዘብ መለወጥ በሚያስችለው አሠራር ማተኮሩ ይበጃል፤›› ነበር ያሉት፡፡ ዶክተሩ ሲቀጥሉ ትልቁና አስፈላጊው ጉዳይ ‹‹ዓሳ አጥምደህ መስጠት ሳይሆን፣ አጠማመዱን ማሳየት›› የሚለውን የአበው ብሂል በማከል ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውም ሆነ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ብሂሉን እንደመርህ ወስደው መቀበል እንደሚያስፈልግ ጭምር ተናግረዋል፡፡

በክብር እንግድነት የተገኙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በበኩላቸው፣ ምርጫው በተሞክሮነት ሊወሰድ የሚገባው መሆኑን ገልጸው፣ የሴቶችን የአመራርነት ሚና በተመለከተ አሁንም ብዙ የሚቀር ነገር መኖሩን ተናግረዋል፡፡

አሁን ባለው የሴቶች ተሳትፎ ትኩረት ተደርጎበትና ተሠርቶበት ሳይሆን በግል ጥረታቸው ወደ አመራር የሚመጡበት ሁኔታ መኖሩ እንደተጠበቀ፣ ነገር ግን ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን ጨምሮ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ሴቶችን ለአመራርነት ማብቃት አሁንም ቀጣይ የቤት ሥራ አድርገው መውሰድ እንዳለባቸው ነው ያስረዱት፡፡

የምርጫውን ሒደት አስመልክቶም ሚኒስቴሩው ግልጽ ፖሊሲ እንዳለ ነው የተናገሩት፡፡ ይኸውም በፖሊሲው አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀፅ 4.1 ላይ እንደተጠቆመው፣ ‹‹የስፖርት ማኅበራት የስፖርቱ መሪ ናቸው›› እንደሚል ገልጸው፣ መንግሥት ከፖሊሲው ውጪ በማናቸውም ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡

ፖሊሲው የመንግሥት ሚናን አስመልክቶ የመደገፍና የማብቃት ሥራ ካልሆነ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ በብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የውስጥ ጉዳይ እንደማያገባውም ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ላይ እንደ ክፍተት ብለው የጠቀሱት ደግሞ በተቋማቱ የሚገኙ ፕሮፌሽናሎችና አማተሮች በአግባቡ ተለይተው የሚንቀሳቀሱበት የአሠራር ሥርዓት አለመኖሩን ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በራሳቸው የውስጥ አሠራር ችግር ሆኖ እየተስተዋለ እንደሚገኝ አልሸሸጉም፡፡

ኦሊምፒያኖች በመከወል በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በሥራ አመራር ቦርዱ የተካተተችው ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ፣ በስፖርቱ ያለፉ ሙያተኞች የአመራርነት ሚና እንዲኖራቸው እየተደረገ ያለው ጅምር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ተናግራለች፡፡source : Ethiopian reporter