Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር የበኩሏን ሚና እየተጫወተች መሆኗን ገለጹ


አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 7 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነት ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ያስቻለ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ፡፡

ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ በአፍሪካ ህብረት እና በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ኢጋድ ያላትን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን እና በሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋት እንዲፈጠር የምታደርገውን ጥረት እንደምታጠናክርም አብራርተዋል፡፡

ከመካከለኛው ምስራቅና እና ከባህረ ሰላጤ ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት የሀገሪቱን ዘላቂ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ይከናወናልም ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ከአውሮፓ፣ አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ጋር ስትራቴጂያዊ ግንኙነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማሳደግ እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ ከቀጠናው ሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት በተለይም የሻዕቢያ መንግስት በድንበር አካባቢ ባሉ ዜጎቻችን ላይ የሚሞክረውን ተደጋጋሚ ትንኮሳ ለመመከት መንግስት ምን እየሰራ ነው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

የመንግስት ስትራቴጂ በቀጠናው ሀገራት ሰላም እንዲኖር ቢሆንም የሻዕቢያ መንግስት ኢትዮጵያን ለማተራመስ እንደሚሞክር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ የሚፈልግ ቡድን በመሆኑ፥ የሰላም ስትራቴጅውን በመጠበቅ ኢትዮጵያን የማተራመስ ሙከራ የሚያደርግ ከሆነ ተመጣጣኝ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት፡፡

ሆኖም በእስካሁኑ ሂደት የሰላም ፍላጎቱ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ያላስመዘገበው የሻዕቢያ መንግስት ለሰላም ፍላጎት ስለሌለው ነው ብለዋል፡፡

የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ፖሊሲ ለማዘጋጀት ጥናቶች መጠናቀቃቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህም መስዋዕት እየከፈለ ያለው ህዝብ ጥያቄ በዘላቂነት ምላሽ ያገኛል ነው ያሉት።

ወደ ኢትዩጵያ በየቀኑ የሚገቡት የኤርትራ ስደተኞች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ወንድሞቻችን እና የእኛ አካል መሆናቸውን በማሳየት ድጋፋችንን ማስቀጠል አለብን ብለዋል፡፡

በዚህ ተግባርም የኢትዮጵያ እና የሻዕቢያ መንግስታት ልዩነት ግልፅ ይሆናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በምህረት አንዱዓለም