አክሱም መጋቢት 8/2009 በትግራይ ክልል አድዋ ከተማ ለህክምና አገልግሎት የተገነባው የፋሻ ማምረቻ ፋብሪካ የማምረት ስራ ጀመረ፡፡
በመንግስት ሆስፒታሎች ብቻ የፋሻ ምርትን ከውጭ ለመግዛት በዓመት የሚጠይቀውን ከ60 ሚሊዮን ብር ወጪ ለማዳን የፋብሪካው መገንባት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የኢትዮጵያ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ገልጿል፡፡
የፋብሪካው ባለቤት አቶ አብርሃም ገብረእግዚአብሔር ለኢዜአ እንደገለፁት በአድዋ ከተማ ከአራት ዓመታት በፊት ያስጀመሩት የፋሻ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ ለማጠናቀቅ 53 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገውበታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ወደ ማምረት ስራ በመሸጋገር ለ54 ሰዎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠራቸውን ጠቁመው ፋብሪካው ለህክምና አገልግሎት የሚውል ያለቀለት ፋሻ ከነግብአቱ በማምረት በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
“በፋብሪካው በተተከሉ ሶስት ማሽኖች አማካኝነት በቀን ለስምንት ሰዓታት እንደሚሰራና በዚህም ጊዜ ውስጥ ከ2ሺህ600 በላይ ጥቅሎችን ያመርታል” ብለዋል፡፡
የፋሻ ምርቱን አሁን መቀሌ ለሚገኘው የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል እያቀረቡ መሆኑን ያመለከቱት አቶ አብርሃም በቀጣይ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ለመላክ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የፋሻ ምርት በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን እጥረት ከማቃለል ባሻገር ሀገሪቱ ምርቱን ለመግዛት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በመቀነስ በኩልም አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
ምርቱ በአገር ውስጥ ካለው ፍላጎት አንጻር አነስተኛ በመሆኑ ተጨማሪ ሶሰት ማሽኖችን በመግዛት አቅርቦታቸውን በእጥፍ ለማሳደግ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የመቀሌ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ገብረማሪያም በበኩላቸው የፋሻ ፋብሪካው የሚያመርተው ለቀዶ ህክምና፣ ለማዋለጃ ፣የደም መፍሰስ ላጋጠማቸው ህሙማን መሸፈኛ ሆኖ የሚያገለግል ግብአት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመንግስት ሆስፒታሎች ብቻ የፋሻ ምርትን ከውጭ ለማቅረብ በዓመት የሚጠይቀውን ከ60 ሚሊዮን ብር ወጪ ለማዳን የፋብሪካው መገንባት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አመልክተዋል፡፡