አዲስ አበባ ፣ የካቲት 28 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በቴሌቪዥን ስርጭት ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ለሚደረገው ሽግግር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚጫወተው የዲጂታላይዜሽን ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱ የሃገሪቱን የቴሌቪዥን ስርጭት ጥራት፣ ተደራሽነትና ደህንነትን የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል።
ስምምነቱ በአሜሪካው ጌትስ ኤር ኩባንያ፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲና በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት መካከል ተፈራርሟል።
ከ34 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቀው ፕሮጀክት፥ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃልም ነው የተባለው።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከ22 በላይ አዳዲስ ቻናሎች እንደሚከፈቱ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጎሳ ደምሴ ተናግረዋል።
አዳዲስ ከሚገነቡት ቻናሎች በተጨማሪም ነባር የስርጭት ቻናሎች ማሻሻያ ተደርጎባቸው ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋልም ብለዋል።
እስካሁንም ፕሮጀክቱን በተመለከተ በኤጀንሲው የሃገራዊ የዳሰሳ ጥናት ተካሂዶ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሲከናወን መቆየቱ ተጠቁሟል።
በአዳነ አረጋ