Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ኢትዮጵያና ሩስያ ሁለት የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራረሙ


አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያና ሩስያ በቱሪዝም እንዲሁም በባህልና ኪነ-ጥበብ ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ለሶስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው የሁለቱ ሀገራት የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ የኢኮኖሚ፣ ሳይንስ፣ ቴክኒክና ንግድ ትብብር ፕሮቶኮል በመፈራረም ዛሬ ተጠናቋል።

ሁለቱ አገራት በጋራ መስራት በሚያስችሏቸው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሶስት ቀናት ሲመክር የቆየው የኮሚሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ በተለያዩ ዘርፎች 12 ጉዳዮች ላይ የጋራ ፕሮቶኮል፣ በሁለቱ ደግሞ የመግባቢያ ስምምነት አርቅቋል።

በዚሁ መሰረት የጋራ ኮሚሽኑ ሰብሳቢዎች ፕሮቶኮሉን ሲፈራረሙ የሁለቱ አገራት የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊዎች ደግሞ የመግባቢያ ስምምነቶቹን ተፈራርመዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትርና የጋራ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ ተገኑ እንዳሉት፥ ስምምነቶቹ አገራቱ በኢኮኖሚና ፖለቲካ ጉዳዮች የበለጠ ተቀራርበው መስራት የሚያስችሏቸው ናቸው።

በሶስቱ ቀን ስብሰባ በበርካታ ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችሉ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን፥ ሁሉም በየዘርፉ ተቀራርቦ በመነጋገር ስምምነቶችን እንዲፈራረሙ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ከዘርፎቹ መካከል ሩስያ በቂ ልምድ ያካበተችባቸውን የማዕድን፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ልማትን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ቪስቮሎድ ኬቼንኮ በበኩላቸው፥ ስምምነቶችን ከማዘጋጀትና ከመፈራረም ባለፈ አብሮ ለመስራት ምቹ የሆኑ ተጨማሪ ዘርፎችን የመለየት ስራም ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።

በማዕድንና ጂኦሎጆካል ሰርቬይ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሁለትዮሽ ንግድ በትብብር መስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች ተጠቃሽ ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አጋጣሚ በአግባቡ ለመጠቀም የአገራቸው የንግድ ማህበረሰብ የሚሰማራባቸው ዘርፎችን ለመለየትም ምክክር መደረጉን ተናግረዋል።

የጋራ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ስድስተኛ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን ሰባተኛ ስብሰባውን ሞስኮ ላይ ለማካሄድ ለሚቀጥለው ዓመት ቀጠሮ መያዙን ኢዜአ ዘግቧል።