የብአዴን መስራች ታጋይ አዲሱ ለገሰ ከጋዜጠኛ አባዲ ገ/ስላሴ እና ሃይላይ ተኽላይ ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ከወይን መፅሄት የካቲት 2009 እትም፡፡
ከኢህዴን ብአዴን መስራች ታጋዮች አንዱ የሆኑት አዲሱ ለገሰ፤ የትጥቅ ትግሉ ካበቃና ደርግ ከተደመሰሰም በኋላ የብአዴን ሊቀ መምበር፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር፣ የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር፣ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስተር፣ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር፣ የፌደራል መለስ አካዳሚ ስልጠና ማእከል ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል። በአሁኑ ግዜም የብአዴንና የኢህአዴግ ምክር ቤት አባል ናቸው።
ወይን፦ ነባር ታጋይና አመራር እንደመሆንዎ መጠን የትግራይንና የአማራን ህዝብ በቅርበት ለማወቅ እድሉ እንደነበርዎት ይታወቃል። በሁለቱም ህዝቦች የነበረውና የቆየው ታሪካዊ ግንኙነት በአሁኑ ጊዜ ያለው ሁኔታ እንዴት ይገልፁታል?
ታጋይ አዲሱ፦ የትግራይና የአማራ ህዝቦች ቀደም ሲል በነበሩት ስርዓቶች ካየነው ሁለቱም ህዝቦች እርስ በርሳቸው የሚጠራጠሩበት ሁኔታ የሚፈጥር ስርአት ስለነበር የገዢ መደብ አመለካከቱ በሁሉም ዘንድ የህዝቦች መቀራረብ የሚፈጥር ባለመሆኑ መጠራጠር እንደነበረበት ግልፅ ነው። ምክንያቱም ስርአቶቹ በህዝቦች መካከል ጥርጣሬ በመፍጠር ነበር የሚያስተዳድሩት። ገዢዎቹ የህዝቦችን አንድነት፣ የህዝቦች መቀራረብ ካለ ህልውናቸው የሚያጥር በመሆኑ ህዝቦች በመከፋፈልና ጥርጣሬ በመፍጠር ነበር የሚኖሩት። ነገር ግን ህዝብ እንደ ህዝብ ሁሉ ጊዜ እርስ በራሱ በሚገናኝበት ጊዜ ጥሩ ግኑኝነት እንደነበረውም በታሪክ የሚታወቅ ነው። አገርን በመከላከል ብዙ ጊዜ አብሮ ተሰልፈዋል። በተለይም ደግሞ የአማራና የትግራይ ህዝብ ጎረቤቶች በመሆናቸው ብዙ የሚያስተሳስራቸው እሴት አለ በሀይማኖት ቢባል፣ በባህል ቢባል፣ በተላያዩ ማህበራዊ ክንዋኔዎች ከተመለከትነው ተመሳሳይ ነው። ከቋንቋ በስተቀር በሌላው አንድ ነው። በዚህ መንገድ ትስስሩ ቀላል አልነበረም። ብቻ ገዢዎች የፈለጉትን ቢያረጉ በህዝቡ መሀከል ያለው ግንኙነት በጋብቻ፣ በማህበራዊ ግንኙነት በንግድ… በብዙ መንገድ በጣም የተሳሰረ ህዝብ በመሆኑ ህዝቦቹ አንድነታቸው ይዘው ዘልቋል።
ትግሉ በሚጀመርበት ጊዜ የነበረው ስናይ ደግሞ፣ ያው በተደጋጋሚ እንደምንገልፀው እኛ ኢህአፓ ነበርን፤ ህብረ ብሄር ነው የነበርነው። ከዛ ነው ወጥተን ወደ ትግራይ የሄድነው። ያ ሲሆን ኢህአፓ እና ህወሐት እስከ ውግያ የሄዱ ድርጅቶች ናቸው። ወጥተን ወደ ትግራይ ስንሄድ ትልቁ ነገር ድርጅቱ ምን ፕሮግራም ይዘዋል? ምን አላማ ይዞዋል? ምን አቋም አለዉ? የሚለው ነበር። ከዚህ አኳያ ህወሓት ሲታገልላቸው የነበሩት ጥያቄዎች ደግሞ የብሄር ጥያቄ፣ የመሬት ጥያቄ የመሳሰሉት ጥያቄዎች በመሆናቸው፣ እኛም ትግሉ ስንጀምር እነኚህ ጥያቄዎች የኛም ጥያቄ ስለነበሩ ድርጅቱ ግን መስመሩ በመካዱ ምክንያት ትግራይ ውስጥ ለመታገል ምቹ ሁኔታ ሊኖር ይችላል የሚል ተስፋ ይዘን ነው የገባነው። ስንገባ የነበረው ሁኔታ ሁላችንም እንደምንገልፀው የትግራይ ህዝብ አቀባበል ከምንም በላይ ለትግል የሚገፋፋ የነበረ፣ አብሮ የሚታገል ድርጅትና ቡድንም ባገኘ ጊዜ ደስታውን በተለያየ መንገድ የሚገልፅ ህዝብ ሆኖ ነው ያገኘነው። በህዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት መለኪያው አንዱ ይሄ ነው።
ከማንም በላይ እኛ እንድንታገል የገፋፋን አንዱ የህዝቡ አቀባበል ነው። ሁለተኛ ድርጅቱ ነው። እዛ በሄድንበት ጊዜ የህዝቡ አቀባበል፣ ከህወሓት ጋር የነበረን አመለካከት በመግለፅ ዙርያ ለበለጠ ትግል የሚያነሳሳ ነበር። በአመለካከት መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች አንድ የነበርን ቢሆንም ግን ደግሞ በሁሉም ነገሮች አንድ በአንድ እየተወያየን ያልተግባባንባቸው መለስተኛ አቋሞችም በሂደት በውይይት እንፈታለን በሚል ነው ትግሉ የጀመርነው። የህወሓት አመራርም በጣም ዴሞክራቲክ እና ጥሩ ነበር። እኛ ትንሽ ነን፤ እነዚህ ሰዎች በትግል ያድጋሉ፣ በትግል እዚህ ይደርሳሉ፣ ህዝባዊ አላማ አላቸው፣ ለትግራይ ህዝብም ይሁን ለሌላው ህዝብ ይጠቅማሉ ብሎ አስቦ ስንደራጅም ስንቀሳቀስም ትልቅ ድጋፍ አደረገልን የትግራይ ህዝብ። ወድያውኑ ትግሉን እንደጀመርንም የትግራይ ህዝብና የአማራ ህዝብ በጣም ተሳስሮ አብሮ የታገለ፣ አብሮ የደማ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም።
ስለዚህ ትግሉ ሲጀመር የነበረው ብቻ ሳይሆን ከዛም በፊት የነበረው የህዝቦች ትስስር ቅድም እንደ ገለፅኩት ሁኖ በትግሉ ደግሞ ይበልጥ በደም የተሳሰረ፣ የትግራይ ልጅ ከአማራ ልጅ፣ የትግራይ ልጅ ከአገው ልጅ ጋራ ሁኖ በአንድ ምሽግ የሚወድቅበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። እና የበለጠ በደም የተሳሰረ፣ ለሰላም፣ ለነፃነት፣ ለእኩልነት፣ ለብሄር ጥያቄ፣ ለሀይማኖት እኩልነት ሲል አብሮ የወደቀ ህዝብ ነውና በደም የተሳሰረ መሆኑ በደንብ መገንዘብ ያስፈልጋል።
ይሄ ሁኔታ አልፎ ተርፎም ለዛ አካባቢ ህዝቦች ነፃነትና እኩልነት ብቻ ሳይሆን አላማው በአገር አቀፍ ደረጃ ዴሞክራሲን ለማምጣትና ለማስፈን ስለሆነ፣ ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ ስለሆነ ከዛ አልፎም ሌሎች ድርጅቶች የሚመሰረቱበት ሁኔታ የፈጠረ ህዝብ ነው፤ የትግራይ ህዝብና ህወሓት። በተለይ ደግሞ ብአዴንና ህወሓት አስቀድመው አህአዴግን የፈጠሩ በመሆናቸው ይሄ በሁለቱ ህዝቦች መሀከል የነበረው ትስስር በጣም ዴሞክራቲክና የአላማ ፅናት ያለው፣ በአንድ አላማ የመዋደቅ ፍላጐትና እምነት እንዲያሳድር የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው።
ወይን፦ ከጥቂት ወራት በፊት በአማራ ክልል አንዳንድ አከባቢዎች በተለይም በሰሜን ጐንደር የተፈፀመውን የጥፋት ድርጊት መነሻውና ምንጩ ምንድነው? በተለይ በመጀመሪያ አካባቢ በተካሄዱ ሰልፎች የነበሩ መፈክሮች ደግሞ ወደ አንድ ደርጅትና አንድ ብሄር ያነጣጠሩ ነበሩ። የዚህ ምክንያት መነሻ ምን ይሆናል? ብአዴን በሚመራው ክልል የተፈጠረው ሁከት ከክልሉ መንግስት ቁጥጥር ውጪ የሆነበት ምክንያትስ ምንድነው? ሁኔታው ሲከሰት ብአዴን አስቸኳይ መፍትሄ ለማስቀመጥና እርምጃ ለመውሰድ የተቸገረበት ምክንያትስ ምን ነበር?
ታጋይ አዲሱ፦ በቅርብ ጊዜ የተፈጠረው ሁኔታ በሚመለከት የአንድ ወቅት ችግር ያመጣው ነው ተብሎ መወሰድ የለበትም። አንደኛ እንደ ሃገር፣ እንደ ኢህአዴግ ምን ነበርን? ምን ገጠመን? እንዴት ፈታነው? የሚል ነገር በደንብ ማየት ያስገልጋል። ከዛሬ 15 ዓመት በፊት ተሀድሶ ነበረን። ወደ ተሃድሶ እንድንገባ ያደረገን ነገር ምንድነው? እንደ ኢህአዴግ ነው ወይስ የአንድ ወይም የሁለት ድርጅቶች ችግር ነው? ብለን በደንብ ማየት አለብን። ኢህአዴግ የትግሉ አላማውን በጠራ ሁኔታ አሳክቷል። ትግሉ ካሳካ በኋላም ወዴት እንደሚሄድም መሰረታዊ ነገሮች አስቀምጠዋል። ነገር ግን እነኝህ ወደ ፊት የምንራመድባቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ዘርዝር ያለ ነገር እይታ ይፈልጉ ነበር። የአመለካከት አንድነት በሚፈጥር መልኩ ግልፅ ለሆነ አላማ የሚወስዱ ነገሮች በደንብ ጥርት ብለው መቀመጥ ነበረባቸው። እነኚህ አለ መቀመጣቸው አንድ ችግር ነበረ። ሁለተኛ በትግሉ ጊዜ የነበረው ዲስፕሊን እና አሰራር በደንብ አሁን ለደረስንበት የዕድገት ደረጃ፣ በከተማም ሆነ በገጠር ከሚገጥመን ሁኔታ፣ የሁሉም አከባቢዎች ህዝብ በትግሉ በተመሳሳይ ያልተሳተፉም ከመሆኑ አኳያ፣ ትግሉ በአንድ ሰሜን ጫፍ ላይ የነበረ ትግል ስለሆነ ሌላ አከባቢ የሚገጥመንን ችግር የምንፈታበት መንገድ የማስቀመጥ ችግሮች ነበሩብን። የዲስፕሊን ችግሮች ነበሩ። ግለሰባዊነት ፍላጎቶች፣ ከትግሉ ወጣ ያሉ አስተሳሰቦች የገጠመበት ጊዜ ነበረ። ከዚህ ጋራ ተዳምሮ የኤርትራ ጦርነት መጣ። በዚህም ችግር ውስጥ ገባን።
ያ ችግር የአንድ ወይም የሁለት ድርጅቶች ችግር አይደለም። የአህአዴግ ችግር ነው። የሃገር ችግር ነው የሆነው። ይሄንን ችግር ለመፍታት በተሀድሶአችን ግዜ ሁሉንም ሰው የችግሮቹ መንስኤ ያነሳ ቢሆንም በተለይ ታጋይ መለስ ዜናዊ እዚሁ ላይ ላነሳው እፈልጋለሁ፣ መለስ በነበረው ችሎታና እውቀት ድርጅቱም ሆነ ሃገርን የሚያድን ሀሳብ በማምጣት ሌላው ሀሳቡን እንዲወስደው በማድረግ መስመራችንን በማጥራት በዛ በጠራ መስመር ታድሰን ወጥተን ተአምራዊ ስራ እንድንሰራ አስችለዋል። ስለዚህ ችግር ይገጥማል። ችግር ሲገጥም በአንዱ ደርጅት ይብሳል፣ በአንዱ ድርጅት ይቀንሳል። እንዲህ ነው ብዙ ጊዜ የሚገጥመን። ይሄ ችግር ከደርግ መውደቅ በኋላ ብቻ የገጠመንም አይደለም፤ በበረሃም ይገጥመን ነበር።
አሁን በሰሜን ጐንደር የታየውም ቢሆን ከዚሁ ጋር በተመሳሳይ መታየት አለበት። ከተሀድሶው 15 አመት ከመጣን በኋላ በሂደት ችግሮች መታየት ጀምረዋል። ድርጅታችንም ሁሉ ጊዜ ፖለቲካዊ ትግል በሚተውበት ለኪራይ ሰብሳቢነት ይጋለጣል። አጀንዳው የህዝብ መሆኑ እየላላ ሲሄድ፣ አጀንዳው የግል ፍላጐት ይሆናል። ይህን ድርጅት የህዝብን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ባልመለሰበት ጊዜ ሁሉ ጊዜ ወደ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አሰራር እየገነነ ይሄዳል። ፀረ-ዴሞክራሲ አሰራር ሲስፋፋ ደግሞ ለኪራይ ሰብሳቢነት በጣም በር ይከፍታል። ኪራይ ሰብሳቢነት እየሰፋ በሚሄድበት ጊዜ በዛው ልክ አድባይነት እየነገሰ ይሄዳል። ይሄ ችግር ነው ትልቁ ችግር። እንደ ኢህአዴግ በተሃድሶ የተቀመጠው ይሄ ነው።
በሰሜን ጐንደር የተከሰተውን ነገር በምናይበት ጊዜም የዚህ ውጤት ነው። ለየት የሚያደርገው ነገር ግን አለ። ምክንያት የሆነ ነገርም አለ። ነገር ግን በጥቅሉ በሚታይበት ጊዜ ኢህአዴግን የገጠመው ዋነኛ ችግር ብለን በተሃድሶ ያስቀመጥነው ነገር ነው በብአዴንም ሆነ በሌላ ድርጅት የመጣ። ሰሜን ጐንደር ላይ ለምን ይሄ መጣ? በሚባልበት ጊዜ ሰበቡ ምንድ ነው? እኔ ሰበብ አድርጌ ነው የምወስደው። ሰበብ አድርጌ የምወስድበት ምክንያት ምንድነው? ጥያቄው አዲስ አይደለም።
የግጨውና ጉቤ የሚባሉት የወሰን ጥያቄዎች ናቸው። እነኝህ የወሰን ጥያቄዎች ከሀያ አመት በላይ ያደረጉ ናቸው። እኔም ክልል እያለሁኝ የተነሳ ጥያቄ ነው። ልክ ትላንት ኮረምም ጠገዴም ላይ እንደፈታነው አሁንም እንፈታዋለን። ቀለል አድርገን ያየነው ጥያቄ ነው የነበረው። ነገር ግን ይህን ለምን ሰፋ የሚለው የራሱ ታሪክ አለው። ሰበብ የሆነው እሱ ነው። መነሻ የሆነውም እሱ ነው። ሁለተኛ መነሻ የሆነው ቅማንት አከባቢ ያለው ጥያቄ ነው። ይሄ እንግዲህ ሰበቡ ነው። መካከለኛ ምስራቅ ቱኒዝያ ውስጥ አንድ ሰበብ ሆኖ የተነሳው ነገር አንድ የዩኒቨርስቲ ምሩቅ ልጅ በእሳት ራሱ ኣቃጠለ፣ ይህ ሰበብ ሆነ። በውስጥ ያለው አመለካከት በህብረተሰቡ ውስጥ ያለ ችግር በትክክለኛ መንገድ ወስደሀው ለትክክለኛ ነገር እንድያደርገው ካላደረግክ በስተቀር መስመር ይስታል። የቅማንት ጥያቄም ተነሳ ሁላችንም እንደምንሰማው እና እንደምናውቀው ቅማንት የማንነት ጥያቄ አነሳ፤ ይሄንን መፍታት ያስፈልግ ነበር። ይህ በምትፈታበት ጊዜ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፍታት አለብህ። አፈታቱ በደምብ በጥልቀት ተጠንቶ መፍትሔ ማግኘት ያለበት ነገር ነው። ሆነም ግን ረጅም ግዜ ወሰደ፤ ይህም አንድ ሰበብ ሆነ።
የጉቤና የግጨውም ተመሳሳይ ነው። ይህም ብዙ ግዜ ተነስቷል። አንድንድ ጊዜ ጫፍ የደረሰበት አጋጣሚም ነበር። ግን አልተፈታም። አሁን ይህን ነገር ባልተፈታ ቁጥር የራሱ ችግር አለው። ህብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጠር ቅሬታ አለ እንጂ ያቺ የግጨውና የጉቤ መሬት የምትባለው አንድ ጫፍ ያለች መሬት ነች፤ ቦታ ነች፤ የጐጃም ሰው፣ የሰሜን ሸዋ ሰው፣ የጐንደር ሰው ወይም የሌላ ሰው ጥያቄ ሊሆንም አይችልም። ምክንያቱም አንድ ሀገር ነን እኛ። እንደ ከኤርትራ ጋር ከሱዳን ጋር ያለ ጥያቄ ሊሆን አይችልም። አንድ ሀገር ነን። ስለዚህ ይሄ በደምብ ታይቶ መፈታት ነበረበት። ለምንድነው ታድያ በወቅቱ ያልተፈታ ሲባል ያው በአመራሩ ችግር ስለነበረ ነው። እዚህ ላይ ምንም መወላዳት የሌለብን ነገር የአመራር ችግር ነበር። አሁን የወሰንዋ ችግር፣ የድንበርዋ ችግር የብአዴን ችግር ብቻ ናት ብየ አላምንም። ይህን ግልፅ መሆን አለበት፣ ስለማውቀው ማለት ነው። ከሁለቱንም አመራር በኩል ያለ ችግር ነው። ይህ ከትግራይ ህዝብና ከአማራ ህዝብ ጋር በፍፁም አይገናኝም።
አመራሮቹ ዴሞክራቲክ በሆነ መንገድ መፍታት ይገባቸዋል። ይህ የኢህአዴግም ግምገማ ነው። ድርጅቱ የሁለቱንም አመራሮች ችግር ነው ብሎ አስቀምጦታል። እዚህ ላይ የትግራይ ህዝብም ግልፅ መሆን አለበት ብየ አምናለሁ። የአመራሩ ችግር ምንድነው? ቅድም እንዳልኩት በውስጥህ ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ሲጠፋ፣ ህዝባዊ አመለካከት ሲጠፋ ምንድነው የሚመጣው? እልህ ነው የምትገባው። ህዝባዊነት ይጠፋል። በህዝባዊ መንገድ አይደለም ለመፍታት ጥረት ሲደረግ የነበረው፣ ነው የምለው እኔ። ያ ነው ችግሩ። ህዝብና ህዝብ በምታይበት ጊዜ ምንም የሚያጣላህ ነገር የለም። ያ ሳይሆን ሲቀር ግን ለትንሽ መሬትም ብለህ ልትዋጋ ትችላለህ። ግን ሊሆን አይችልም። የወሰኑ ጉዳይ ከዚህ በፊትም ከሀያ አመት በፊት እየተነሳ ይሄ ትንሽ ነገር ነው እያልን ነው የተውነው። በግልፅ ለመናገር መፈታት ነበረበት። ማቆየታችን የሁላችንም ችግር ነው፣ በእኔ እምነት። ሁላችንም ያለንበት ችግር ነው። ግን ይህን ወደ ግጭት ወደ ምናምን ይወስዳል ብየ ግን አላምንም። ወደ ግጭት ለምን ሄደ? እውነት ያ መሬት የሚያጋጭ ስለሆነ ነው? አይደለም። ግን ቅድም እንዳልነው በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው ችግር አማራ ክልልም ትግራይ ክልልም አለ። ብዙ ስራ ያጣ ወጣት አለ። በቀላሉ በስሜት ሊቀሰቀስ የሚችል ወጣት አለ። ይሄ በአንድ በኩል በአመራር ውስጥ ያለውን የአመለካከት መዛባት የፈጠረው ነው። ይሄ መዛባት በሚፈጠርበት ግዜ ይህን ጥያቄ አንስተህ ተበድያለሁ ብለህ ትግራይ ነው እንደዚህ ያደረገኝ፤ በዚህ በኩል የትግራይ የበላይነት አለ፤ በዚህ በኩል ደግሞ ትምክህት አለ የሚል አመለካከት በሁለቱንም ጫፍ በሚገኝበት በአመራሮቹ ውስጥ ወዴት ነው የሚወርደው? ወደ ታች ነው የሚወርደው። ወደ ስራ አጥቶ ስሜት ውስጥ ያለውን ወጣት ነው የሚወርደው። አንዱ ይሄ ነው ያጋጠመው።
ሁለተኛ በርህን በደምብ ካልዘጋህና በውስጥህ በርህ ዘግተህ ችግርን ፈትተህ ካልወጣህ፣ በርህን ክፍት ካደረግከው ያው ማንም መንገደኛ ይገባል። ፀረ ህዝብ ገባበት፤ ጐራ ተደበላለቀ። ህዝብና አመራር የሚለይ፣ ጥፋተኛና ጥፋተኛ ያልሆነው የሚለይ ጠፋ። በአመለካከትም ጐራው ተደበላለቀ። ያው የገመገምነው ነው። እንደ ብአዴንም ገምግመነዋል። ይሄ ጐራ መደበላለቅ ይዘህ በምትመራበት ጊዜ እኮ ዞሮዞሮ ህዝቡ በስሜት ወደ ያልሆነው ነገር ይገባል። ያ ነው የሆነው። ትምክህተኞች ሰማይ ሰቅለው ሊጠቀሙበት ሞከሩ። በጣም የከፋውና አስቀያሚው ነገር መጀመርያ የተጀመረው ቅማንት ላይ ነው። ቅማንት ከኛ ጋር አብሮ የታገለ ህዝብ ነው። ይህን ህዝብ ጥያቄ አንስቷል። ይህ ሲሆን እነሱም ውስጥ ጫፍ የሄዱ ሰዎች ይኖራሉ። ሁሌ አንድ ነገር በሚነሳበት ወቅት ጫፍ የሚሄድ አካል አለ። የትኛውም ቦታ፣ የትኛውም ድርጊት ውስጥ። ግን ጫፎቹን አይደለንም ማየት ያለብን። ማየት ያለብን የጉዳዩን መሰረታዊ ጉዳይን ነው። ባለቤቱ ደግሞ ህዝብ ስለሆነ፣ ህዝቡን ይዘን ነው የምንፈታው። ታድያ የሆነውን ነገር ምንድነው ቅማንት ውስጥስ? ቅድም እንዳልኩት ቅማንትም ውስጥ “እኔ የቅማንት ኮሚቴ ነኝ የሚለው አካል የራሱ ችግር አለበት። የኛም የአፈታት ችግር አለ።
አንደኛ ቅማንት ያለው አማራ ክልል ውስጥ ነው። ሌላ ቦታ አይደለም ያለው። ራሱ ቢችልም እኛው ጋር ነው። ልክ እንደ አዊ፣ እንደ ዋግ ኽምራ እንደ በአማራ ክልል ውስጥ ያለው የኦሮምያ ልዩ ዞን እንደ አርጐባ ነው የሚሆነው። ከፈታህ እንደዛ ነው የምትፈታው። ይህን ሁኔታ አንኳን አይደለም ወደ ግጭት ልያመራ ቀርቶ ኮሽ ሳይልም ልትፈታው ትችላለህ። የመፍታት ልምዱ ደግሞ አለ። ብአዴን ለእንደዚህ ጥያቄ አዲስ አይደለም። ምናልባትም በጣም ብዙ ልምድ የሚገኝበትና የአመራር ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት እንዲያብብ እንዲጐለብት፣ ለማድረግ አስተዋፅኦ ያለው ነው ብዮ ነው የማስበው። በውስጡ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦችን በአግባቡ በመያዙ፣ ጥያቄያቸውን ዴሞክራቲክ በሆነ መንገድ በመፍታቱ ነው። የቅማንትም ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ነው መታየት ያለበት። ይህ ሲሆን የብአዴን ዴሞክራሲያውነት ነው የሚያሳየው፣ ህዝባዊነት ነው የሚያሳየው። ሌላ ምንም ነገር አያሳይም። እዚህ ላይ ስህተት እየተፈጠረ መጣ።
ስህተቱ እዚህ ላይ ብቻ አልነበረም። የቅማንት ጥያቄ ከትግራይ ጋር ተያያዘ። የቅማንት ጥያቄና ከትግራይ ጋር ያለው የድንበር ጉዳይ የሚያገናኘው ነገር የለም። ግን ተገናኘ። ፀረ ህዝብ በምትሆንበት ጊዜ መያያዝ የማይቻለውን ነገር ታያይዛለህ። “ድምበሩን የወሰዱት የበላይነታቸው ተጠቅመው ነው፣ ቅማንትም እያደራጁ ነው” ምናምን በሚል አንድ ላይ ያው የውጭ ጠላትም ገባ ማለት ነው። ጐራ ተደበላለቀ። አመራሩም ቶሎ ቶሎ በውስጡ እርምጃ እየወሰደ ከመሄድ ይልቅ እንዲሁ እየተጠማዘዘ ቆየ። ይህ ምን አመጣ? በቃ ትግራይ ነው እየበደለ ያለው የሚል አይነት ነገር መጣ። በህዝቡ መሀከል በፍፁም ተደርጎ የማይታወቅ፣ ዓይነት ስሜት እንዲፈጠር ሆነ። ይህ ነው በጣም ቆሻሻው ነገር የሚመስለኝ። የቅማንት ጥያቄ ብአዴን ራሱ መፍታት የሚገባው ነገር በትግራይ ሲሳበብ ይሄን በአመለካከት መዋጋት ያስፈልግ ነበር። ትክክል አይደለም። የድንበሩም ቢሆን ይሄ በላይነት ምናምንቴ ሳይሆን የወሰን ጥያቄ ነው መፈታት አለበት ተብሎ መካሄድ አለበት። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከአንዳንድ የህወሓት አመራሮችን ነገሩ እንዴት እንደዚህ ሆነ፣ እንዴት ተደፈርን የሚል አስተሳሰብ ነበረ። ይሄ ግልፅ ነው፣ መታረም አለበት።
ነገር ግን አንድ አመራር በሚናገረውና በሚያሳየው ጉዳይ ህዝባዊ ባልሆነ መንገድ አይደለም የምትመዝነው። ይሄ ችግር ነበረው። ለማንኛውም ሰልፍ የተደረገበት ቀንም እንደዚህ ሆነዋል ተብሎ ሲነገረኝ ነው የሰማሁት እንጂ አላወቅኩም ነበር፣ በኋላ ሄጄ አይቸዋለሁ። በጣም የሚያሳዝን ነው። በአይንህ ልታየውም በጀሮህ ልትሰማውም የሚከብድ ነው። በብአዴንም ደረጃ እንደዛ ይሆናል ብለህ የምትገምተው አይደለም። የድርጅታችን ባህሪም አይደለም፤ ከደርጅታችን ጋር የሚሄድ ተግባርም አይደለም። ፀረ ህዝቡን አጀንዳውን ወስዶ ያ አመለካከት አሁን በዛ አከባቢ የበላይነት ወስደዋል። አሁን ድርጅቱ የበታች ሆነዋል። ህዝባዊ አመለካከቱ ጠፍቶ የፀረ ህዝብ አመለካከት የበላይነት ይዟዋል። በዛን ጊዜ የተነሱትም መፈክሮች “ቅማንቶች ብአዴንን አንፈልግም ብሏል” በሚሉ የብአዴን ጠበቃ ሆነው ነው የቀረቡት፣ ያኔ ሲቀርቡ። ሰልፍ ሲመጣ ግን የብአዴን ጠበቃ እንዳልሆኑ በግልፅ ተረጋግጧል። መፈክራቸው ስታየው የወልቃይት ጉዳይ፣ ተነስተው የማያውቁ የሱዳን ድንበር ጉዳይ፣ የያዙት ባንዴራም የኢትዮዽያ እውነተኛው ባንዴራ ሳይሆን የድሮው ባንዴራ ተይዞ ነው የተወጣው። ስለዚህ ምን ለማለት ፈልጌ ነው፣ በደርጅቱ ውስጥ ችግር በሚኖርበት ጊዜ ፀረ ህዝብ አመለካከት ነው የበላይነት የሚይዘው።
በድርጅቱ ውስጥ፣ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አሰራር ካለ አድርባይነትና ኪራይ ሰብሳቢነትን የበላይነቱን እየያዘ ነው የሚሄደው። ስለዚህ በዛን ወቅት ዴሞክራሲያዊ አመለካከት የሚባል ነገር የለም፣ ጠፍቷል። ፀረ ህዝብ አመለካከት ነው የበላይነት የያዘው። ያኔ ፀረ ህዝብ አመለካከት ለምን የበላይነቱን ያዘ ለሚለው፣ ያው ቀደም ሲልም በተሃድሶአችን እንደተቀመጠው አመራሩ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ችግር መሆኑ በደምብ መታወቅ አለበት። የያኔ መፈክር ፀረ ትግራይ ህዝብ ብቻ አይደለም። ፀረ አገርና ህዝብ ነው፣ ፀረ ህገ መንግስቱም ነው። የትግራይ ህዝብ ብቻ አይደለም የሚመለከተው። የህወሓት የበላይነት አለ በሚባልበት ጊዜ የበላይነቱን የሚገለፅበት ጉዳይ ካለ መቀመጥ አለበት። ድርጅቱ እንደዛ ዓይነት አስተሳሰብ አለዉ እንኳን ቢባል ህዝብ እንደ ህዝብ አይባልም፤ ተብሎም አያውቅም። ነውር ነው። ያን ብልሽት ይህን አምጥቷል። በነገራችን ላይ አንዱ ብሄር ከአንዱ ብሄር ጋር በሚጋጭበት ጊዜ አንዱ ብሄር ብቻ አይደለም እኮ ህይወቱ የሚጠፋው። ሁለቱንም ነው። በቅማንትና በአማራ መሀከል በነበረው ግጭት ሁለቱንም ነው የተሰዉት። ከሁለቱንም ብዙ ህዝብ አልቀዋል። ከሁለቱንም ብዙ ንብረት ወድሟል። ምክንያቱም አንተ የሌላውን መብት እጋፋለሁ ብትል ያንተን መብት እንደማይከበር ማወቅ አለብህ። የሌላውን መብት እስካከበርክ ብቻ ነው ያንተው መብት የሚከበረው። ይሄ ነው የብአዴን/ኢህአዴግ አመለካከት።
ስለዚህ ያ ትምክህተኛ ሰልፍ ትምክህት የተጠናወተው ሰልፍ ነው። ህዝባዊ ሰልፍ አይደለም። አመራሩ ለምን ይህንን አልፈታም? ከእጁ አምልጧል። አሁን ሰው ያንን ሰልፍ ምናምን ነው የሚለው። ሰልፉ መጀመርያ ማስቆም ይችል ነበር። በየወረዳው በየቀበሌው ማስቆም ይቻላል። ህዝቡን ይዘህ ማስቀረት ትችላለህ። ነገር ግን በውስጡ አመለካከቱ ካለ የት ታስቀረዋለህ። ስለዚህ ያመጣው አመለካከቱ ስለነበር ይህን እንደምንም ለማብረድ ተሞክሯል።
ይህ እንግዲህ የትግራይ ህዝብ ከቅማንት ጋር አትለው፣ የትግራይ ህዝብ ከአማራ ህዝብ ጋር አትለው የድርጅቱ የራሱ ችግር ነው። ምንም ጥያቄ የለውም። አጀንዳውም ፀረ ህዝቡ ነጥቆ ወስዶበታል። + ለምሳሌ አንድ ቦታ ግጭት ይነሳል፣ ሰው ይፈናቀላል። ነገር ግን በህዝቦች መሀከል ፍቅር ስላለ በሚፈናቀልበት ጊዜ እንዳይፈናቀል ይጥራል፣ ይሸፍናል። አሁን በብአዴን አከባቢ በሰሜን ጎንደር የሆነው ጉዳይ ግን በጣም ከመቼውም ጊዜ በላይ ብልሽቱን የሚያሳየው፣ የትግራይን ሰውን ማፈናቀል ነው። አዲስ ነገር ነው። በተለይ በብአዴንና በህወሓት መሀከል መሆኑ ነው እንጂ፣ የአማራ ህዝብ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ከኦሮምያም በሺዎች በአስር ሺዎች ነው የተፈናቀለው። ይህንን ይታወቃል። ይህ ሲሆን ስንል የነበርነው ድርጅቱ አይደለም፣ ህዝቡ አይደለም፣ አመራሩ ነው ብለን ነው የምንለው። በቁጥር የተፈናቀለው አይገናኝም። ብዙ ጊዜ አንዴም አይደለም፣ ከአንድም ሁለት ሶስት ግዜ ተፈናቅሏል። ነገር ግን ኦህዴድ ሆኖ ወይ እገሌ ነው፣ ብለን አናውቅም። ፀረ ህዝብ አመለካከት ያላቸው፣ ህዝባዊ አመለካከት የሌላቸው አመራሮችና መጥፎ ጥገኛ ሰዎች የሚያደርጉት ድርጊት ነው ብለን ነው የምንወስደው። አሁንም እኔ እንደዛ ነው የምመለከተው።
የብአዴን መርህ አይደለም። አይደለምና አብሮ የደማው፣ አብሮ በአንድ ምሽግ ውስጥ የወደቀው የትግራይ ታጋይና ህዝብ ቀርቶ ማንንም ህዝብ ማፈናቀል አላማም ተግባርም ያልነበረው ደርጅት ነው ብአዴን። እሱ እታገልለታለሁ የሚል ህዝብ እንኳን እንደዛ ሲሆን መአት ትምክህተኛ፣ ብዙ በሚልበት ጊዜ አንድም ጊዜ ሰምታችሁ አንደሆነ አላውቅም። እገሌ እንዲህ አደረገን ብለን አናውቅም። ብአዴን እንደዛ ብሎ አያውቅም፤ ምክንያቱም ድርጅትን ያህል ነገር ስለሆነ እንዲህ የሚያደርገው። ድርጅት እንደ ድርጅት ይህን የሚያደርግ ከሆነ እኮ ድርጅት የሚባል ነገር የለም፣ አብቅቷል። ከድርጅቱ ውስጥ የተወሰኑ አመራሮች ልያደርጉ ይችላሉ። አስተሳሰቡን የሚቀበል ሊኖር ይችላል። ህዝቡ ግን እንውሰደው፣ የጐንደር ህዝብ ያን መፈናቀል ሲመጣ እኮ፣ እኔ እስከማውቀው ድረስ አንድ ቀን አውሮፕላን ሲሳፈሩ እዛው ስለነበርኩኝ ለሁለቱንም ለአማራም ለትግርኛ ተናጋሪዎቹም ሰብስቤ አናግርያቸው ነበር። የህዝቡ አይደለም። ፀረ ህዝብ አመለካከት የበላይ ስለወሰደ ነው።
የህዝቡ ግንኙነት ከአመራሩ ግንኙነት የተለየ ነው። የህዝቡ ግንኙነት ከልብ ነው። አብሮው ነው የኖሩት፣ አብሮው ነው ያደጉት፣ አብረው ደግኑም ክፉንም ያዩ ህዝቦች ናቸው። በተለይ ጐንደር ውስጥ። ድሮም ቢሆን እኮ ጐንደር ውስጥ ከትግራይም ብዙ ነበር፣ ትግርኛ ተናጋሪው በጣም ብዙ ነው። አብሮ የሚኖር ነው፤ የተጋባ ነው ሁለተኛ በሃይማኖትም አንድ ነው፤ በባህልም አንድ ነው። ብዙ ነገር፣ ከቋንቋ ልዩነት በስተቀር በአማራና በትግራይ መሀከል ምንም ልዩነት የለም። ልዩነቱ ቋንቋ ብቻ ነው። ሃይማኖቱ ቢሆንም ክርስቲያን ከሆነ ክርስቲያን ነው፣ እስላም ከሆነም ተመሳሳይ ነው። ይህ ስለሆነ እኮ ያ ሁሉ ችግር እያለ ከመጀመርያ ጀምሮ እስካሁን ያልወጣ በርካታ ሰው እንዳለ ይታወቃል። በጣም በርካታ ህዝብ አሁንም አለ። እስኪ ምን እንሆናለን ብለው፣ ህዝቡን ተማምነው፣ የቀሩ አሉ። ንብረት መውደምም በተመለከተም የአንድ ሰውም ንብረት መውደምም አይገባም ነበር፣ ግን እንደሚባለው አይደለም።
አሁን አማራ በቤንሻጉልም በኦሮምያም በሌሎችም ንብረቱ የሚወድምበት፣ ህይወቱ የሚጠፋ ብዙ ነው። በጣም በርካታ። ግን እንደዛም ሆኖ እዛም እየደበቁ የሚያሳልፍዋቸው ህዝቦች አሉ። እኛ ነው የምናበላሽ እንጂ በህዝቦች መሀል ያለ ትስስር የማይነቃነቅ ነው። አንዳንደቹ በጎንደር ውስጥ በግርግሩ ወቅት ከወገኖቻቸው ወግነው እኮ “ናስኪ ድፈረኝ፣ አትነካውም” ብለው ወገንነትታቸው ያሳዩም አሉ። ይህ በደምብ ይታወቃል። እና ይሄ በትግራይ ህዝብ ዘንድ የተፈጠረው ነገር ያው ቅድም እንዳልኩት ከባድ ነው፣ ያማል። ይህንን በተለይ በሁለቱንም ድርጅቶች የነበረውን ግንኙነት ሲታይ በሁለቱ ህዝቦች በነበረው ግንኙነት ሲታይ ህዝቡ ለምን ተሰማው አልልም። መጥፎ ስራ ስለተሰራ መሰራትም ስላልነበረበት፤ መደረግ ያልነበረበት ድርጊት ስለተደረገ፣ በጣም አስነዋሪ ድርጊት ስለተፈፀመ። ተግባሩ መጥፎ መሆኑ በጣም መታወቅ አለበት። የትግራይ ህዝብ ቢሰማው እኔ አልፈርድበትም። ከሆነ በኋላ ግን ያው ዞሮ ዞሮ ይሄ ነገር መለወጥ አለበት። ግን በዚሁ ጉዳይ የትግራይ ህዝብ ማመን ያለበት የሚመስለኝ እሱም ይናገረዋል፣ የህዝቡ አይደለም።
የአመራሩ፣ ብልሹ አመራር የተሳተፈበት፣ ብልሹ አመራር ሲባልም ሁሉም የብአዴን አመራርም አይደለም። በዚህ ላይም ስህተት እንዳይፈጠር ግንዛቤ መውሰዱ ያስፈልጋል። ስለዚህ የትግራይ ህዝብም መረዳት ያለበት ብአዴን እንደ ብአዴን ይህንን ያደርጋል የሚል አመለካከት መያዝ አለበት ብየ አላምንም። እንደዛ ቢሆንና የብአዴን አመራር ሁኔታው ለመፍታት ባይጥር ችግሩ አይቆምም ነበር። ይህን ጉዳይም መታየት አለበት።
ሶስተኛ ላነሳው የምፈልገው፣ እንዲህ ዓይነት ነገርስ ለምን መጣ? በሚባልበት ጊዜ ፀረ ህዝብ አመለካከት ለምንድነው ወደ ህዝቡ የሚሰርፀው? ብለን በምናይበት ጊዜ፣ መማር ያለብንም ጉዳይ ያለ ይመስለኛል። እዚህ ላይ የአማራ ጥገኛ አመለካከት ያለው፣ አማራ ተበድለዋል በሚል ለመሸቀጥ ለመነገድ የሚፈልግ አለ። በነገራችን ላይ “ከትግራዎት” ውስጥም እንደዚሁ ጥገኞች አሉ። ሳይታገሉ እንደታገሉ መሬት የሚለቅሙ ሰዎች አሉ፣ በግልፅ ነው የምናገረው። እዚሁ አዲስ አበባ ቁጭ ብለው ልክ እንደ ታገለ ሰው ታግለናል እያሉ በኪራይ ሰብሳቢነት የትግራይን ህዝብ ከህዝብ የሚነጥሉ፣ ሁሉንም ትግራዋይ እንደነዛ ሰዎች የሚያስመስሉ፣ ምንም ሳይኖረውና ደግሞ “እኛ ነን ታግለን እዚህ ያበቃናችሁ” እያለ የሚፎክር፣ ባለጌ አለ። ይህንን በተሀድሰውም አይተነዋል። ለትግራይ ምንም ሳይጠቅም፣ አንድ ድንጋይ ሳይወረውር፣ ለትግሉም ምንም ነገር ሳያደርግ እሱ እዚህ አዲስ አበባ ቁጭ ብሎ በየከተማው በህገወጥ መንገድ እየከበረ የሚሄድ ጥቂት ሰው አለ። ይህን ጥቂት ሰው ደግሞ ተከትሎ፣ የተጠቀመ መስሎት እሱም የሚለውን ነገር የሚልም ሰው አለ። ይሄ አደገኛ ነው። ለትግራይ ህዝብ አይጠቅምም። ይህንን መታገል ይጠይቃል። ብአዴንም መታገል አለበት፣ ህወሓትም መታገል አለበት፣ የትግራይ ህዝብም መታገል አለበት።
የትግራይ ህዝብ ኑሮውን አውቃለሁ፣ ደሙ ተፍቶ ልጆቹን ገብሮ ለሀገር ነፃነትና እኩልነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ ህዝብ ነው፤ ምንም ጥያቄ የለውም። ብዙ ነገር ተሸክሞ፣ ብዙ ነገር ከፍሏል። ነገር ግን ይሄ ሸክሙን ይህንን በጐ ምግባሩ የሚያንቋሽሹ ደግሞ በውስጡ አሉ። በአማራ ውስጥ ያለ ጥገኛ ትምክህተኛም ይሄው እንዲህ እያደረጉ ናቸው እነሱ ይላል። እነኝህን ጥቂቶችን እንደ አብነት እየወሰደ ነገሩን ለማባባስ ይጠቀምበታል። የትግራይ ህዝብን አይደለም የሚያየው።
ስለዚህ እነዚህ ሁለቱንም ትግል ያስፈልጋቸዋል። ነገር ግን አሁንም አስምሬ ማስቀመጥ የምፈልገው የትግራይም ህዝብ የአማራም ህዝብ ሊነጥለው የሚችል ነገር ሊኖር አይችልም። ህዝቡ ሁሌ ይኖራል። አመራር ሊቀያየር ይችላል። ህዝቦች ግን ሊነጣጡሉዋቸው፣ ሊያኖራቸው የሚችል አመራር ሊኖር አይችልም። ስለዚህ ይሄ ግንኙነት ወደ ትክክለኛው መመለስ አለበት። የሚመለሰው ደግሞ አንደኛ እነኝህ ሰበብ የሆኑትን ነገሮች ማጥፋት ያስፈልጋል። ሰበቦቹ እነዛ የድንበር የምናምን የሚባሉት መጥፋት አለባቸው። ዋነኛው ግን እሱ አይደለም። ዋነኛው እያንዳንዱ ድርጅት ወደ ትክክለኛው፣ ወደ ህዝባዊነቱ መመለስ አለበት። በቃ እኔ የማምነው እንደዛ ነው። በእልህ በፉክክር በምናምን የሚፈታ ነገር የለም። ትልቁ መፍትሄ ፖለቲካዊ ነው። ትልቁ መፈትሄ ህዝባዊ ውግንናን መሰረት አድርጐ የሚነሱ ጥያቄዎችን መፈታት ነው። በህዝባዊ ውግንና ዓይን የምንፈታ ከሆነ በሁለቱም ድርጅቶች መሀከልም ይሁን በሁለቱም ህዝቦች መሀከል የማይፈታ ችግር የለም። ይህንን መነሻ አድርጐ መፈታት ይገባል እላለሁ።
ከዚህ አኳያ ድርጅቱ እቅድ የያዘ ይመስለኛል። ወደ ፊት ህዝቡን አወያይቶ ከጨረሰ በኋላ በሁለት ህዝቦች መሀከል በሁለቱ ድርጅቶች መሀከል ውይይቶች ይኖራሉ ተብሎ ተቀምጠዋል። እኔ እስከማውቀው እንደዛ ነው የማየው። ትግል ይፈልጋል፣ ግን ይፈታል ብየ አምናሎህ።
ወይን፦ እንደሚታወቀው በኢህአዴግ ደረጃ የተካሄደው በጥልቀት የመታደስ መድረክ አለ። ከዚህ በመነሳት ብሄራዊ ድርጅቶቹም የየራሳቸው መድረክ እያካሄዱ ቆይቷል፤ እየቀጠሉበትም ነውና እርስዎ እንዴት ይገመግሙታል። እስካሁን በነበረው ጉዞ ብአዴንስ ውስጡን ያየበት መንገድ እንዴት ነው የሚገለፀው?
ታጋይ አዲሱ፦ ከዚህ በፊት መመለስ ያለብኝ አንድ ጥያቄ አለ። የወልቃይት ጥያቄን የተመለከተ። ወልቃይትን በሚመለከት እኔ ክልል ከነበርኩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የብአዴን ጥያቄ ሆኖ አያውቅም። ግልፅ መሆን ያለበት፣ የትግራይ ህዝብም ግልፅ መሆን ያለበት የሚመስለኝ፣ ሁሉም ህዝብ ግልፅ መሆን ያለበት በወልቃይት ብአዴን ጥያቄ አንስቶ አያውቅም። ግለሰቦች ወደ ውጪ የወጡ ሰዎች ምናምን ያነሱታል። ግን ይህን በምንም ተአምር ብአዴን ጥያቄ ነው ብሎ አንስቶት አያውቅም። ወልቃይት በድሮው አከላለል ከሆነ ጐንደር ውስጥ እንደነበረ ይታወቃል። አሳይታም ወሎ ውስጥ እንደነበረ ይታወቃል እኮ። የድሮው ጂኦግራፊያዊ ወይም መልከአምድራዊ አከላለል ቀርቶ በብሄር ሲሆን ወልቃይት ትግራይ ውስጥ እንደተደራጀ ግልፅ ነው።
ሌሎች ሳነሳቸው የነበርኩት አከባቢዎችም አሁን ወዳሉበት ቦታ ተካልሏል። ነገር ግን የወልቃይት ጥያቄ እያሉ የሚያነሱ የወልቃይት ሰዎችም ሌሎች ፀረ ህዝብ ቡድኖችም እንዳሉ ደግሞ እናውቃለን። ግን የኛ ጥያቄ ሆኖ አያውቅም። በጥያቄ መነሳት ዓይን ከሆነ እኮ የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነት የማይቀበል ጥያቄ አለ። አንቀፅ 39 ይነሳ የሚልም አለ። ሰለዚህ ከመጀመርያው ጀምሮ ይህን ጥያቄ ይነሳ ስለነበረ አሁንም መነሳቱ ትክክል ነው የሚል ሰው ስህተተኛ ነው እላለሁ። በአጠቃላይ ግን የወልቃይት ጥያቄን ብአዴን እንደ ብአዴን አንስቶት አያውቅም። ዛሬም አጀንዳው አይደለም፤ በጣም ግልፅ መሆን አለበት። የትግራይ ህዝብም ግልፅ መሆን አለበት። ጥያቄ ያነሱ ቡድኖች አሉ። ጐንደር ውስጥም ብዙ የወልቃይት ሰዎች አሉ፤ ማንም የማይክደው ገሃድ ነው። ወደዛ የመጡ ነጋዴዎች አሉ። ይህንን ጥያቄና የወልቃይት ጥያቄ ግን ይለያያል። ምን ያህል የወልቃይት ሰው በሽሬ ወይ በሌላ የትግራይ አከባቢዎች አሉ ቢባል በጣም ትንሽ ነው የሚሆነው። “አፊሌሽኑ” ወይም ዝምድናው ጐንደር ውስጥ አለ። ይሄ ዛሬ አይደለም የታወቀው፣ ድሮም የነበረ ነው። ኤርትራዊ ጐንደር ውስጥ ነበረ፣ ድሮ በነበረው ታሪክ ሄዶ ማለት ነው። የትግራይን የጐንደርን ህዝብን ብዛት በምትመዝንበት ግዜ እኮ ቀላል አይደለም። ከትግራይና ኤርትራ በጣም ብዙ ሰው ነበር። እንደዛ ነው ማየት ያለበት። ዝምድናው ለስራም ለምናምንም ወደ ጐንደር ነው ያለው።
ይሄና ሌላው ግን ይለያያል። ይሄ ማለት ለምሳሌ ከምሴ ጋር ሄደህ እዛ ጥግጥግ ያሉ አማራዎች ከሚሴ ውስጥ ነው ኢንቨስት የሚያደርጉት። ወደ ሌላ ቦታ አይሄዱም። የሚሄዱት ወደ ከሚሴ ነው። ሌላውም እንደዛ ነው የማየው። እንደውም አንድ ጊዜ ምን ሆነ? እዛ ሰሜን ሸዋ አንዲት ጣምቢት የምትባል ወረዳ ነበረች። ለብቻዋ ነበረ አስተዳደር ይዛ የቆየችው። ከዛ ከከሚሴ ጋር ነው የምንሆነው የሚል ጥያቄ አነሳች። ይህንን ስታነሳ በእልህ ነበር ያነሳችው። በወቅቱ ጥያቄውን የማንፈታው መስሎዋቸውም ነበር። ከዛ በኋላ የከሚሴ አስተዳደር ዞን ምንድነው ችግራችሁ ብሎ አነጋገራቸው። ወረዳ እንሁን ነው፤ ከሆንን እዚህ እንሆናለን አሉ። ስለዚህ አንድ አንድ ጊዜ በህዝቦች መሀከል የሚኖረው ጥያቄ ምንድነው ብሎ አድምጦ መፈታት ይፈልጋል።
ወደዚህ ቅሬታ የወሰደው ምንድነው ማለት ያስፈልጋል። ምን ለማለት ፈልጌ ነው የወልቃይት ህዝብም እንደ ሌላው ህዝብ ቅሬታዎች እንዳሉት አውቃሎህ። የመልካም አስተዳደር የልማት ችግር ነበረበት ቀደም ሲል። እኔ ድሮ ወደ ወልቃይቶች ሄጄ ባነጋገርኩባቸው ጊዜ የሚያነሱት እነዛ ችግሮችን ነው። እኔም እዚሁ መጥቼ ጓደቼን ስነግራቸው እውነታቸው ነው፤ ነው ያሉኝ። እና አንዳንድ ጊዜ ኩርፍያም ወደ ሌላ አማራጭ እንድታይ ያደርጋል። እኔ ምክንያቱን ይሄ ነው ሊሆን የሚችለው ብየ ነው የምገምተው።
ከዛ በተረፈ ግን የህወሓት አባላትንም የትግራይ ህዝብንም ማወቅ ያለበት የወልቃይት ጉዳይ የብአዴን ጥያቄ አይደለም። የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ አለበት እንኳን ቢባል ጉዳዩ የሚመለከተው ለህወሓት ነው። ለትግራይ መንግስት ነው የሚመለከተው። የትግራይ መንግስትም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ህዝቡን አግኝቶ፣ ቅሬታውን ፈትቶ መያዝ አለበት የሚል እምነት አለኝ። ከዛ በላይ ደግሞ ያው ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ነው፤ ስርዓት ነው፣ በስርዓት መስተናገድ አለበት። በዚህ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች እንደሚሰጡ የታወቀ ነው። ግን አሁንም መሰመር ያለበት ጉዳይ ብአዴን ወልቃይትን ጥያቄ አድርጐ ተነስቶ አያውቅም። ዛሬም ነገም ሊያደርገው አይችልም። ለህዝቦች እኩልነትና ህገ-መንግስታዊ መብት የሚጠይቅ ካለ ግን የትኛውም ቦታ ያለውን ህዝብም ሆነ አካል በአግባቡ ማንሳት ይችላል።
ወይን፦ የጐንደርን ሰልፍ በተመለከተ የብአዴን አመራር በቸልታ ስለተመለከተው ነው እንጂ ሰልፉ በዛ ደረጃ ላይሆን ይችል ነበር። ህጋዊ ሰልፍም ስላይደለ መቅረት ይችል ነበር። ከዚህ በተጨመሪ ሰልፉ እንደተካሄደም ህጋዊ የሚያስመስሉ መግለጫዎች ከአንዳንድ የብአዴን አመራሮች ይሰጥ ነበር። የወልቃይት ጉዳይም ቢሆን የብአዴን ጥያቄ የሚያስመስሉ መግለጫዎች ይሰሙ እንደነበረ የሚታወቅ ነውና ይህንን እንዴት ነው የሚገልፁት?
ታጋይ አዲሱ፦ አመለካከቱ የተበላሸ አመራር የሚናገረውም ንግግርም እኮ መበላሸቱ አይቀርም። ያችን ብልሽቱን እኮ ነው የሚገልፀው። አሁን የግጨውና እዛ ጠገዴ ኣከባቢ የጉቤ ጥያቄ አለ። ጠገዴና ወልቃይት ደግሞ ያው አንድ ላይ ናቸው፣ አንድ ህዝብ ነው። ጥያቄው ከመነሳቱ በፊት እዛ ሲደራጁ እንደነበረም ይታወቃል። አመራሩ ይህን ሁኔታ በቸልታ እየተመለከተው ቆይቷል። “መብታቸው ነው፣ ምን ተቃዋሚዎች ይደራጁ የለም እንዴ? ይደራጁ” እየተባለ በቸልታ ታልፈዋል። ድርጅቱ ይህን ትክክል አይደለም ተብሎ ሂስ ግለ ሂስ አድርጐበታል።
ስለዚህ ይህንን ለምን ተፈጠረ ተብሎ በስሜት መረዳት የለብንም። ወጣቶችም ጥያቄውን እውነት ነው ብለው ተቀብለው በስሜት ሲንቀሳቀሱ እኮ ህይወታቸውም ከፍሏል። ይህን የሆነው ሁኔታው መጀመርያ ወደ ያልሆነው መንገድ እየሄደ እንዳለ እየታወቀ ዝም ስለተባለ ነው። ጥያቄውን የሚያነሱ ሰዎች ተደራጅተው ኦፊስ ሲከፍቱ ብትፈልጉ ወልቃይት ውስጥ ወይ ሌላ ትግራይ ቦታ ክፈቱ መባል ነበረባቸው። ምክንያቱም የትግራይ መንግስት ከከለከላቸውም በህገ-መንግስታዊ መንገድ መብታቸውን ማስጠበቅ ስለሚችሉ። ይህንን ሲሆን ግማሹ በቸልትነት ምን አለበት ብሎ የተመለከተው አለ። ሌላው ደግሞ በንቃት ቢደራጁ መብታቸው ነው የሚያስከብሩት ብሎ የሚሟገት ነበረ። ትግራይ ውስጥ አላስከፍት ስላልዋቸው እዚህ ከፈቱ የሚሉ አሉ። ይህን ሲሆን መዘዙ በደንብ ማሰብ ያስፈልግ ነበር። ከዚህም ውጭ ድንበራችን ጠገዴ የሚባለው ሳይሆን ተከዜ ነውም እኮ ተብለዋል። ይህን የድሮውን ጂኦግራፊ ማለት ነው። ይህ ማለት ምን ማለት ነው ከተባለ አንቀፅ 39 አለመቀበል፣ መቃወምን ነው የሚያመለክተው። ይህን ከስር መሰረቱ ማየት ካለብን ወጣቶቹ እንደዛ ሲሉ የነበረ እውነት ስለመሰላቸው ነው። ግን ስህተት ምን ግዜም ሊኖር ይችላል። አሁን የአማራ ወጣቶች ሲሳሳቱ የትግራይ ወጣቶች ምን ማድረግ ነው ያለባቸው? ወደ እልህ ነው መግባት ያለባቸው? ወደ የት ይደርሳሉ ነው መባል ያለባቸው? እንደዛ ማለት የለባቸውም። ተሳስቷል፣ ይህንን መታረም አለበት ነው ማለት ያለባቸው። የትግራይ ወጣቶች ቢሳሳቱስ እነሱን ነጥሎ ማረም ነው የሚሻለው ወይስ ህዝቡን እንደ ህዝብ ነው መፈረጅ ያለበት። አንድ አደገኛ መታረም ያለበት ጉዳይ ይሄ ነው።
አንዳንድ ቦታ እንደሚባለው የህወሓት የበላይነት ስላለ ይሄው እነዚህ ለህወሓት ተማምነው እንደዚህ እያደረጉ ናቸው ይላሉ። አሁን እነዛ ወይ ቡድን ናቸው ወይ ግለሰብ ነው። የትግራይ ህዝብ አይደለም። ትግራይን እንደብሄር የምትጠላበት መሆን የለበትም። የአማራ ወጣትም ይህንን መረዳት አለበት። አሁን እኛን እያሳሳተን ያለው ይህንን ነው። አንድ ኦሮሞ ቢያጠፋ፣ ሁለት ኦሮሞ ቢያጠፋ፣ የሆነ ነገር ቢናገር ኦሮሞ በሙሉ ሊፈረጅ አይችልም። የኦሮሞ ህዝብ እንደዚህ ነው ማለት አይገባም። ነውር ነው። ልክ እንደዛ ስለ አመራሩም ብዙ ነገር ሲባል እሰማሎሁ፣ አነባለሁ። አመራሩም ሊሳሳት ይችላል። ዋናው ነገር የተሳሳተውን አመራርስ ከስህተቱ ተማረ ወይ የሚልም ጠቃሚ ነው። ከስህተቱ ከተማረ ያው መሳሳትማ ሊያጋጥም ይችላል። ማንንም ቢሆን ሳይሳሳት እኮ የመጣ የለም። ተሳስቶ ከስህተቱ ከተማረም ማድነቅ ነው ያለብን። ሁሉንም እየተሳሳተ ግን ከስህተቱ እየተማረ ነው እዚህ የደረሰው።
አንድ ነገር ግን ጥሩ የሚመስለኝ፣ የትግራይ ህዝብ በሳል ነው። በትግሉ በስሏል። አንዳንዴሞ ሚድያ ስለምከታተል እነኝህ የተፈናቀሉትን ሰዎች ሲናገሩ ሰምቻቸዋሎሁ፣ አስተዋይ ናቸው። እዚህ ጎንደር ውስጥም አሉ አማራዎች በተፈጠረው ሁኔታ ሌት ተቀን የሚያለቅሱ። በሁኔታው በጣም ያዘኑ፣ በጋብቻ የተጋቡ በብዙ ነገር የተሳሰሩና ለብዙ ጊዜ አብረው የኖሩ። የትግራይ ወጣትና ህዝብ ማወቅ ያለበት ይህንን ነው። የአማራ ህዝብ ለትግራይ ህዝብ ያለው አመለካከት ምንድን ነው? ብሎ ማወቅ አለበት። ጐንደር ውስጥ ያለው አማራ በጣም ጥቂቱን ነው የትግራይ ሰዎች እንደዚህ አደረጉን ዓይነት ስሜት ያንፀባረቀ ወይስ ብዙሀኑን ነው። ይህንን በደንብ መለየትና መገንዘብ ካልቻልን መጥፎ ነገር ወደ ትውልድም እናስተላልፋለን።
ስለዚህ የትግራይ ወጣትም ቢሆን ህወሓትም ቢሆን ሁኔታውን በደምብ መገንዘብ ያስፈልጋል። ብአዴንም እንደዚሁ። አሁን ያለውን አመራር ዘላቂ አይደለም። ተረካቢው ወጣት ነው። ወጣቱ ምንድነው የሚረከበው? የተፈጠረውን ስህተት በታሪክ ይዞ በመጠርጠር ይሁን? ወይስ ብልሹ አመራር የፈጠረውን ስህተት ታግሎ፣ አስተካክሎ ትክክለኛውን ታሪክ ነው መረከብ ያለበት? በእልህና በእናሳያቸዋለን መንፈስ ከሆነ ሁኔታው ለሁለቱም ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነትም እንበለው ለአገሪቱም ጥሩ አይደለም። ስለዚህ አመራሩ ችግሩ የቱ ጋር ነው ያለው ብለን፣ ቁጭ ብለን መፍታት አለብን። ስህተቱ የአንድ ወገን ብቻ አይደለም። በሁሉንም ስህተት አለ። ምናልባት ያንዱን ያይል ይሆናል። ቅድም እንደገለፅኩት እስከማፈናቀል የሄደው ስህተት ያይላል። ይህ ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ያ የወሰኑ ጥያቄ ሁለት ሶስት ቀበሌ እንኳን የማይሞላው በእውነት አገር ሙሉ ሊያበጣብጥ የሚችል ነው? ከተባለ ግን ይህንን በአግባቡ በመረዳት መፋታት ያስፈልጋል። ይህን ጉዳይ አስተዋፅኦ ስለነበረው በወቅቱ መፈታት ነበረብን ለማለት ነው።
የተሃድሰውን በሚመለከት ድርጅታችን በበረሃም እያለ በየወቅቱ፣ በየምዕራፉ ተሃድሶ ያካሂድ ነበር። ተሃድሶ ሲካሄድ ድርጅቱ አንድ ችግር ሲገጥመው፣ ድርጅቱ ውስጥ ያልሆነ ዝንባሌ ሲፈጠር፣ ወይ ወደ ፊት ለመራመድ በአስተሳሰብ በተግባርም የሚቀይድ ነገር ሲገኝ ለምን እንደዚህ ሆንን ብሎ ያያል። አሁን ተሀድሶ ካካሄድን 15 ዓመታት ሞልቶናል። ከዛ በኋላ የመጡ ነገሮች አሉ። እድገት አምጥተናል። እድገቱ የፈጠረው ችግርም አለ። በብዛት ስራ አጥ ወጣት አለ። ይሄ ስራ አጥ ደግሞ ስራ ካላገኘ ወዴት እንደሚሄድ ይታወቃል። ሌሎች በወቅቱ ማረም የነበረብን ነገሮች ነበሩ፤ አላረግነውም። የዛሬ አራት አምስት አመትም ጥያቄዎች ይነሱ ነገር፤ መለስም እያለ። እሱም ሁሌ ሲለው እንደነበረ የተማረ ወጣት በብዛት ባለበት ሕብረተሰብ ውስጥ ስራ ከሌላው ምን ሊመጣ እንደሚችል ያስቀመጣቸው ነገሮች አሉ። ይሄን አደጋ በደምብ ለይተን በተለይ የስራ አጥነትን በሚመለከት ብዙ ርቀት አልሄድንምና መፈታት አለበት። በአገሪቱ ከመጣው እድገት አብዛኛው ወጣት የሚጠቀምበት ሁኔታ የምንፈጥርበትን አቅጣጫ ብናስቀምጥም በሚገባ አልሄድንበትም። ዋነኛው ችግር ይሄ ነው።
ሁለተኛው ኢኮኖሚው በጣም እያደገ ሄደ፣ እሱን እያየን የውስጣችን ፖለቲካዊ ሁናቴ በደንብ አላየንም። ውስጣዊ ብልሽታችን እየተከመረ፣ እየተከመረ ነው የሄደው። ድሮ ችግሮቻችን በወቅቱ እንደታዩ ወድያውኑ እየፈታን ስለምንሄድ ቀይደው እስከሚይዙን አንጠብቅም ነበር። አሁን ግን አብዛኛውን ኢኮኖሚውን ብቻ እያየን የመልካም አስተዳደሩም፣ የፖለቲካ ስራውም፣ ዕለታዊ ትግሉ ቆም ነበር ማለት ይቻላል። ይሄ ያመጣው ውጤት ነው ለዚህ ያደረሰን።
እንዳው ከአማራ በፊት እኮ ሕዳር ውስጥ ኦሮምያ ውስጥ ነበር አንዳንድ ችግሮች የታዩት። ቀጥሎ ወደ አማራ ሄደ፤ ከዝያ ውድያ ችግሩ እንደ ሃገር ሆነ። የመልካም እስተዳደር ችግር ሃገር አቀፍ ችግር ነው የሆነው። የትኛውም ክልል የመልካም አስተዳደር ላይ፣ ዴሞክራሲያዊ አሰራር ላይ ጥሩ ነኝ የሚል አንድም የለም፣ ሊኖርም አይችልም። ታጋይ በነበረው ሕብረተሰብ፣ ትግራይም ውስጥ የሚነሳ ጥያቄ ነው። አመራሩ ደግሞ ይሄን ጥያቄ በወቅቱ ለመመለስ የሚጥረው ነገር ብዙ የለም። ይሄ እንግዲህ ቅድም ባልኩት ነገር ሲገልፅ፣ ይሄን መቀየር፣ መለወጥ ያስፈልጋል፤ መታደስም ያስፈልገናል የሚል ነገር ተቀባይነት አግኝቶ ተጀምሯል። ይሄ ተሃድሶ፣ እኔ በጅምር ደረጃ ጥሩ ነው። ጅምር ነው ብየ ነው የምወስደው፣ ጅምሩ ጥሩ ነው። ግን ጅምሩ ጥሩ ነው እያልክ ብቻ መሄድ ደግሞ ተገቢ አይደለም።
ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች አሉት። በመልካም አስተዳደር እንበለው ሊፈቱለት የሚችሉ መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ። በተሃድሶ አካሄዳችንም ተሎ ተሎ ልንፈታቸው የምንችላቸውን ተሎ ከስር ከስር መፍታት አለብን ነው ያልነው። ጎን ለጎን ግምገማችን እያካሄድን፣ ሂሰና ግለሂሱም እየተካሄደ፣ እየተራረምን፣ ጐን ለጐን ደግሞ የህዝቡ ጥያቄዎች እየተፈቱ መሄድ አለባቸው ነው ያልነው። አሁን እንደዛ ነው ወይ በሚባልበት ግዜ ግምገማው ብዙ ጊዜ ነው የወሰደው። አሁን በግምገማው ረዥም ርቀት እየሄድን ነው ያለነው። አሁን በየቦታው አንዳንድ እርምጃዎችም መወሰድ ተጀምሯል። የህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎች ግን መፍታት እየተጀመሩ ናቸው እንጂ አልተፈቱም። እንግዲህ እዛ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል። ተሃደሰው እውነተኛ እንዳስቀመጥነው ጥልቅ እንዲሆን ከተፈለገ ህዝቡ አመኔታ አሳድሮ እውነትም ችግራችን ይፈታል እንዲል የሚያደርግ እርምጃ መኖር አለበት የሚል እምነት አለኝ። ከቦታ ቦታም ይለያያል።
እንግዲህ ተሃድሶ ከተባለ ምህረት የለሽ መሆን አለበት። በእኔ እምነት ብልሽታችን ደግሞ ከላይ ከአመራር ነው ብለናል፣ ከታች አይደለም። ስናርምም ከላይ መሆን አለበት። ያለርህራሄ ለማረም መጣር አለብን። ጥልቅ ተሃድሶ ከሆነ ማለት ነው። እዛ ላይ የተጀመሩ ነገሮች ናቸው ያሉት፣ በእኔ እምነት። ምክንያቱም ኪራይ ሰብሳቢነት ብለን ብዙ ጮኾናል፤ ብዙ አንስተናል። ያው ህዝቡም ሰምቶናል ማለት ነው። እንዲህ ዓይነት ተሃድሶ ድፍረትና ጥንካሬን ይፈልጋል። ህዝባዊ ውግንናን ይዘህ ለማንም ምህረት ሳታደርግ መጀመርያ በአመለካከት አተኩረህ ትሰራለህ፣ በተግባርም መጥፎ ተግባር ውስጥ ያለን እርምጃ ትወስዳለህ። ይሄ መኖር አለበት። ጥልቅ ተሀድሶ ማንንም የሚምር መሆን አይችልም። በአመለካከቱ መቀየር፣ መለወጥ ያለበት ሰው በአመለካከቱ መቀየር አለበት። በተግባሩ ብዙ ጉዳት ያደረሰ ከሆነ በዛው ልክ እርምጃ መውሰድ አለበት።
ህዝቡ እንግዲህ ከኛ በላይ መነፅር ነው። ከኛ በላይ ማን ምን እንደሆነ ያውቃል። አንድ ብዙ ግዜ የምንዘነጋው ነግር ይሄ ነው። ህዝቡ ያውቃል። አሁን ኪራይ ሰብስቧል የሚባል አመራር ማን ነው ብትለው ያውቀዋል። ግን መጀመርያ አንተን ያያል። መጀመርያ አንተን ቁርጥ ያለ አቋም ይወስዳል ወይ ብሎ ይፈትሸሃል። የምትወስድ ስትሆን ይበረታታል። “ይሄው እዚህ ጋም እገሌ አለ እንደዘህ አድርጓል፤ እንደዚህ አድርጓል” ይላል። ያውቃላ! ሕብረተሰቡ የሚኖርበት ስለ ሆነ ያውቃል። ይሄ ብሄር ሳይለይ፣ ማንነትን ሳይለይ፣ መወሰድ ኣለበት። “Confidence build” ማድረግ የሚቻለው መተማመን የሚፈጠረው እንደዚህ ሲሆን ነው።
ለምሳሌ የአማራ ጥገኛ ካለ፣ የአማርኛ ዘብ ጠበቃ መስሎ የሚናገር ካለ ትለየዋለህ። ፊትለፊት መታገል አለብህ። ፊትለፊት ማጋለጥ አለብህ። የሚማር ከሆነ እንዲማር ታረገዋለህ። የማይማር ከሆነ ደግሞ በሚማርበት መንገድ ታስተምረዋለህ። በኦሮሞ፣ በደቡብ ካለ እንደዚሁ፣ ትግራይም ካለ እንደዚሁ መደረግ ኣለበት። በእኔ እምነት የኔ ብሎ የሚሸፈን ነገር መኖር የለበትም። እንደዚህ ሲሆን መተማመን ይፈጥራል። በድርጅቶች ማሀከል መተማመን ይፈጥራል፤ በህዝቦች መሃከል መተማመን ይፈጠራል።
አንድንዴ የውሸትም ወሬ እኮ ሀገር ይፈታል፣ የሌለ ነገርም ይወራል እኮ። ግን የውሸትም ይሁን የእውነት የተነሳ ነገር ካለ በግልፅነት፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ፣ ህዝብ እንዲያውቀው እያደረክ ከሄድክ፣ የድርጅት መድህን ማለት እሱ ነው ለእኔ። ኣልበለዝያ ህዝብ የሚያየውና የሚያውቀው ነገር ሌላ ኣንተ የምትናገረው ሌላ ከሆነ ግን ኣደገኛ ነው። ስለዚህ ተሃድሶው በተቀመጠለት አቅጣጫ ግቡን እንዲመታ ከተፈለገ ግልፅነት፣ ተጠያቂነት፣ መኖር ኣለበት። የውሸትና የእውነት ነገሮች ተለይተው እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል። እዚህ ላይ ህዝበ ያግዛል፤ ምንም ጥያቄ የሌለው ነገር ያግዛል። ቅድም እንዳልኩት ነው። በህዝብ ስም ብዙ ነገር ይደረጋል። አማራ ተበደለ እያለ አማራን የሚበድል አለ፣ ኦሮሞን ተበደለ እያለ ኦሮሞን የሚበድል አለ፣ ትግራይ ተበደለ እያለም ትግራይ የሚበድል እንዳለ መረዳት ያስፈልጋል። ይሄነው እንግዲህ ግልፅ ወጥቶ፣ መድረክ ላይ ወጥቶ መታረም ያለበት የሚመስለኝ። ተሃድሶአችን ወደዚህ አይነት ደረጃ መሄድ አለበት።
እታች ያለው ቀላል ነው ለኔ። እታች ያለው በተለይ ወደ ህዝቡ የቀረበ ስለሆነ በግልፅ ህዝቡ እራሱ ያግዛል። የወረዳ አመራርን ብትወስደው ህዝቡ እከሌ፣ እከሌ፣ እከሌ እንደዚህ ናቸው ብሎ ለመናገር ምንም አይቸግርም። ለመሸፈንም እድል ያለው የላይኛው ነው፣ ለኔ። ብዙ መሸፈኛ አለው። ሁለተኛ በፌደራል ደረጃ ያለ ደግሞ የበለጠ ለመሸፈኛ እድል አለው። ምክንያቱም ከየትኛውም ብሄር ይሂድ አያውቀውም ሕብረተሰቡ። አዲስ አበባ ያለው ነው የሚያውቀው። እዛ ባለው ብሄሩ ስም ግን እሱ እዚህ ይነግዳል፣ ጠበቃ ይሆናል። ግን እሱ ንሮውን ያመቻቻል፤ በሌብነት ይገባል፤ በመሳሰሉት። እንግዲህ አይነቱ ቦታ እንዳይኖረው ማድረግ ያስፈልጋል።
እንደዚህ ሆኖ ግን ተሀድሶ ማለት በአንድ ጊዜ፣ በአንድ ውይይት የሚያልቅ ነገር አይደለም። ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ገና ጅምር ነው። እኔ አሁንም አሳምሬ የምናገረው ጅምር ነው። ገና በደንብ መጥለቅ አልጀመረም። መጥለቅ አለበት። መጥለቅ ደግሞ ሲባል ቅድም እንዳልኩት፣ የህዝቡን ጥያቄዎች በመመለስ ነው። ዝም ብሎ እንመልሳለን ብሎ ቃል በመግባት ሳይሆን አሁን የሚመለሱትን፣ ችግር የሌለባቸው፤ መመለስ የምንችላቸውን መመለስ። ጊዜ የማይሰጡ ቅድሚያ ሊሰጡ ሚገባቸውን ለይቶ መመለስ መቻል ለህዝቡ ያስፈልጋል።
ሁለተኛ ለወጣቱ በመንግስትም በሚድያም ሁላችንም እየሰማን ነው፤ እናንተም እየሰማችሁት ነው። “እንዲህ እንዳርጋለን እንደዚህ እናረጋለን ”ተብሏል። አሁን መፍጠን፣ ወጣቱ ስራ አጥቶ “ዳቦ” ነው እያለ ያለው። ሌላ ጥያቄ የለም። ወጣቱ ሲወያይ ኮ የወልቃይት ፀገዴ ምናምን የሚባለው ነገር አይደለም ያለው “ዳቦ” ነው ያለው። እኛ እኮ ሲወያይ አይተነዋል። ወጣቶቹ ጥያቂያቸው ዳቦ፣ ቤት፣ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀን ስራ የለንም፣ ይሄን ነው የምንፈልገው ነው የሚለው። ይሄን መመለስ ያስፈልጋል። ስለዚህ መመለስ የምንችለው ፈጥነን መመለስ በጣም ተገቢ ይመስለኛል።
ወይን፡- በመጨረሻ ለትግራይ ህዝብ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?
ታጋይ አዲሱ፡- ያው እንደገለፅኩት የትግራይ ህዝብ ዛሬ ለደረስንበት ዴሞክራሲ ዛሬ ለደረስንበት ዕድገት ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ከፍተኛ ነው ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ሚና የተጫወተ ህዝብ ነው። እዚህ ላይ መሰመር፣ መታመን ያለበት ይመስለኛል። ሁሌም የምለው ነው፣ ልጁ ያልሰጠ፣ ንብረቱ ያልሰጠ ህብረተሰብ የለም። በግልፅ እንደሚገለፀው ከ 60 ሺ በላይ ልጆቹን ያጣ ህዝብ ነው። ስለዚህ ይሄ ህዝብ ታጋይ ህዝብ ነው። ዛሬም ራሱ ለመቻል እየተፍረጨረጨ ያለ ህዝብ ነው። ይህን አድርጌለሁና ይህን ይከፈለኝ ሳይል ወገቡን አስሮ ዛሬም ተራራ እየቧጠጠ፣ ውሃ እያቀበ፣ አፈር እያቀበ ኑሮውን ለማሻሻል ሌት ተቀን የሚጥር ህዝብ ነው። ታታሪ ህዝብ ነው። ለቡዙዎች አብነት የሚሆን ህዝብ ነው። እዚህ ላይ አንድ መጨመር የምፈልገው የትግራይ ህዝብ እስካሁንም እንደ ህዝብ ያለፈለት ህዝብ አይደለም። እኔ እስከማውቀው ድረስ ህዝቡ እንደህዝብ ያለፈለት አይደለም። ሁሌ የምለው ነው፣ ገጠሩን ያለ ህብረተሰቡን ያላየ ሰው፣ ብዙ ነገር ልይል ይችላል።
ብዙ ግዜ በአመለካከትም በተግባርም ያጋጠሙት ችግሮች አሉት፣ የትግራይ ህዝብ። ይህን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድና በትግል አሸንፎ ወጥቷል። አሁን በተፈጠረው ብአዴን በሚመራው ድርጅትና አከባቢ፣ ብህወሓት በሚመራው አከባቢ የተፈጠረው ችግር ግዚያዊ ነው። በምንም ተአምር ከዚህ በፊት የነበረንን ግንኙነት ሊያጠፋው የሚችል አይደለም። ስለዚህ ብአዴንም ሆነ ህወሓት ሁለቱ ድርጅቶች በአመለካከትም በተግባርም ህዝባዊነትን ይዘው በሁለቱም ህዝቦች መሀከል እየታየ ያለውን የመጠራጠር ስሜት ለማስወገድ እየሰሩ ናቸው። መስራትም ይገባቸዋል።
እንግዲህ ያለፈ ነገር ብዙ ጊዜ ለዛሬና ለነገ ትምህርት ይሆናል እንጂ አንዴ የሆነ፣ በተግባር የተፈፀመ ነገር አይመለስም። ነገር ግን ለዛሬም ለነገም ትምህርት መሆን አለበት። በተለይ ወጣቱ ትውልድ፣ የትግራይ ወጣት ቅድም እንደገለፅኩት፣ የተፈጠረውን ሁኔታ በአንድ መንግስት ወይም ድርጅት ውስጥ የአመለካከት ችግር በሚኖርበት ጊዜ የተግባር ችግርም አብሮ እንደሚከተል መገንዘብ ያስፈልጋል። ይሄ ለትግራይ ህዝብ አዲስ አይደለም። የአመራር ችግር በሚኖርበት ግዜ በቀጥታ ህዝቡ ላይ ይንፀባረቃል። ልክ በትግራይ ውስጥ ያለው የመልካም አስተዳደር፣ የዴሞክራሲ ችግር እዚህም እንዳለ መታወቅ አለበት። ህዝቡ በነዚህ ችግሮች ጥያቄዎች አሉት። ልዩነቱ ምንድነው? ጫፍ የሄደውን ነገር ነው። እንጂ መነሻው ያ እንደሆነ መገንዘብ አለብን። ሁለተኛ የአማራ ህዝብ በስሙ ብዙ ነገር እየተፈፀመ ነው። በአጋጣሚ ሆና ያለፉት ገዢ መደቦች በስሙ ብዙ ነገር ሰርቷል። የአማራን ህዝብ ያልሆነውን ሆንክ ብለው ለብዙ ነገር ዳርጎውታል። ወገኖቹን ወንድሞቹን እንዲጠራጠር ብዙ ነገር ጥረዋል። ሁሉም በድህነት ውስጥ እያለ፣ በአስተሳሰብ ግን እሱ የበላይ እንደሆነ፣ ብልጥ እንደሆነ እያሞካሹ ሌላውን በበጐ ዓይን እንዳያየው ሲሰሩ ኖረዋል። ነገር ግን የአማራ ህዝብ ከሌላ ህዝብ የተለየ ጥቅም ሲያገኝ የነበረ ህዝብ አይደለም።
ይሄ የትግራይ ህዝብ በደንብ ያውቀዋል። ወጣቶችም ማወቅ ያለባቸው ይህንን ነው። አሁንም ቢሆን መጠኑ ቢለካ ብዙ ከድህነት ወለል በታች ህዝብ ያለበት አማራ ክልል ነው። እንደማንኛውም ህዝብ ያልፍልናል ብለው ተራራ እየቧጠጡ የሚኖሩ ህዝቦች እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል። ስለዚህ በዓይነ ህሊና መምጣት ያለበት ህዝቡ ነው። ይህን ህዝብና የራሱን ህዝብ አንድ ላይ ማየት ያስፈልጋል። ሁለቱንም እዚህ ላይ ልዩነት የላቸውም። አመራሮች ግን ይህን ሁኔታ በትክክል እንዳይገነዘብ የምያደርጉ ይኖራሉ። ትክክለኛ አመለካከት ያላቸው አመራሮች የሚገነዘቡት ግን ይህንን ነው። በትግራይ ህዝብና በአማራ ህዝብ ምንም አይነት ልዩነት እንደሌለ ይገነዘባሉ። ለሁለቱንም ለውጥ ይሰራሉ። ለሁለቱንም ዕድገት ይሰራሉ። የኢህአዴግ ዓላማም፣ ግብም ይሄ ነው። ህዝቦች እንድያልፍላቸው፣ ሌሎች ያደጉ አገራት ህዝቦች የደረሱበት የኑሮ ደረጃ እንዲደርሱ ነው የሚሰራው። በዚህ ዓይን መመልከት አለባቸው።
አሁንም የትግራይ ህዝብ ይህንን ጊዝያዊ ችግር እንደምንሻገረው፣ በትግርኛ አባባል ነበረው “ፀገማት ክንሰግሮ ኢና” ይል ነበር ድሮ አንድ ችግር በሚፈጠር በት ጊዜ። “ክሓልፍ እዩ እቲ ፀገም” ይል ነበር ድሮ። አሁንም እንደዛ ነው። ይህንን ችግር አልፎ ለበለጠ በጋራ የአማራ ህዝብና የትግራይ ህዝብ ከሌላውም ህዝብ ጋር ሆነው ይህቺ አገር ማድረስ ወደምንፈልግበት ደረጃ ያደርሳሉ። ቅድም እንደገለፅኩት የተፈፀሙት ድርጊቶች በጣም አጠራጣሪና ነውርም እንደሆኑ ደርጅታችን ብአዴንም ገምግመዋል። ችግሩን በማቃለል ረገድ ግን ችግሩ በአንድ ጀምበር ቁርጥ ብሎ አይሄድም። አሁንም የሚያዩት፣ የሚገነዘቡት ነገር ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ትግል ሂደት ነው፣ ለትግራይ ህዝብ መልሼ ላስተምር አልፈልግም። ችግር የሚሆነው ትግል ሂደት ነው እየተባለ ከተተኛበት ነው። ነገር ግን በየጊዜው ለውጥ እንዲመጣ የምያደርግ እርምጃና ተግባር እስካለ ድረስ በሁሉም ህዝቦች መሀከል አሁንም፣ የጠነከረ ስራ የጠነከረ ግንኙነት ይኖራል ብየ እገምታለሁ። አሁን ውይይቶቹ እያለቁ ናቸው፤ ሁለቱም ህዝቦች የማገናኘት ስራ መሰራት አለበት። ስለዚህ በትግራይም በኩል ግፊት መደረግ አለበት ብየ አምናለሁ። አንዳንዴ ጥፋቱ አየል ያለበት ሀይል ጥፋቱን ማርገብያ ነገር ይፈልግ ይሆናል። ነገር ግን ህዝባዊ ስትሆን ጥፋት የተሰራበትም እንዲመለስ ነው መጣር ያለበት። ምክንያቱም ተባብሶ ሌላ ነገር እንዲመጣ አይደለም የሚፈለገው። ቅድም እንዳልኩት ነው፣ ለአሁኑ ትውልድም ይሆን ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፈው ጥሩ ነገር መሆን አለበት። መጥፎ ነገር መሆን የለበትም። የትግራይ ህዝብም በዚህ ዓይን እያየ ነው ያለው። አሁንም በጣም ጨዋና ትክክለኛ አቋም ይዞ እየሄደ ያለ ህዝብ ነው። ህዝቡን ነው የማወራው እኔ።
አሁንም ይሄ ነገር በሰላማዊ መንገድ እንዳያልቅና ሁለቱ ህዝቦች በቂም እንዲተያዩ የሚፈልግ ደግሞ አለ። ከሁለቱም ይህን ነገር እያባባሰ የአማራ የአመራር እና አማራን ህዝብ ለይቶ የማያይ አስተሳሰብ ያለባቸው ሰዎች አሉ አሁንም። ምክንያቱም ከሁለቱም ግጭቶች እንጠቀማለን የሚሉ ሰዎች አሉ፣ በሁለቱም። የትግራይ ህዝብ ይሄን ማወቅ አለበት። ሌላውም ህዝብ ይህን ማወቅ አለበት። የሁለቱም ህዝብ ግጭት፣ የሁለቱም ህዝብ መጠራጠርና በጎሪጥ መተያየት ለማንም አይበጅም። ህዝብን ነው የምንጎዳው። በዚህ የሚጠቀሙ ግን ግለሰቦች ይኖራሉ። እነዚህን ግለሰቦች በዚህም፣ በዛም ያሉ፣ በብአዴንም በሌላውም ያሉ እየታገልን በጋራ እንደድሮአችን፣ እንደጥንቱ፣ እንዳሳለፍነው ጊዜ ሁለቱ ህዝቦች በጋራ ሆነን፣ ለሌላውም አርአያ ሆነን የምንታይበትን ሁኔታ ነበረ እስከ አሁን። ያ ሁሉ መተማመን አሁን ጠፍቷል፣ በሌሎች ድርጅቶችም ቢሆን፣ በኢህአዴግም አባላት። ጥያቄም ያነሳሉ። ድሮ ሁለቱም ድርጅቶች ጠበቅ ብለው በሁለቱ ህዝቦች መሀከል ያለው ግንኙነት ምን እንደሚመስል እያሳዩ ሌላውም በዛ አርአያነት እንዲሄድ ያደርጉ ነበር። አሁንም የትግራይ ህዝብ የአማራም ህዝብ ወደዛ ዓይነት መንፈስ ውስጥ ተመልሶ መታየት አለበት። ለሌላውም አካባቢ አርአያ ሆኖ፣ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም እንደዛ እንዲሆን ትልቅ ምኞቴ ነው። ይሆናልም ብየ የምተማመንበት ነው።
ወይን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በወይን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስም ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን።
ታጋይ አዲሱ፡- እኔም አመሰግናለሁ።