Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በኦሮሚያ ‹‹የኢኮኖሚ አብዮት›› የመጀመሪያ ለሆነው ኩባንያ 617 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖች በግማሽ ቀን ተሸጡ


ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አክሲዮኖቹን መግዛት ይችላል ተብሏል
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በቅርቡ ይፋ ባደረገው ‹‹የኦሮሞ የኢኮኖሚ አብዮት›› ውስጥ በቅድሚያ እንዲመሠረት የተፈለገውን ኦዳ ትራንስፖርት ኩባንያ ለመመሥረት በግማሽ ቀን በተካሄደ የአክሲዮን ሽያጭ፣ 617 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖች መሸጣቸው ታወቀ፡፡

የኩባንያው አደራጅ ኮሚቴ አባል፣ የኦሮሚያ ክልል የመሠረተው የመንግሥት ባለሀብቶች ጥምረት ምክር ቤት አባልና የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታከለ ኡማ ያልተጠበቀ የአክሲዮን ሽያጭ በግማሽ ቀናት ብቻ መከናወኑን፣ ይህ ደግሞ ቀድሞ የታሰበው ዝቅተኛ መመሥረቻ ካፒታል ሊከለስ እንደሚገባው ማሳየቱን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የአክሲዮን ሽያጩን ይፋ ለማድረግ መጋቢት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የተጋበዙት ተሳታፊዎች 700 ብቻ እንደነበሩ የገለጹት አቶ ታከለ፣ የኦሮሞ ባህል ማዕከል አዳራሽ ሞልቶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በዚህ ቀን በተካሄደ ሽያጭ ከ154 ሺሕ በላይ አክሲዮኖች በመሸጥ 617 ሚሊዮን ብር መገኘቱን አስረድተዋል፡፡

ታዋቂ ባለሀብቶች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ተማሪዎች እንዲሁም መካከለኛ ባለሀብቶች ግዢውን መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ የተገኙት ታዳሚዎች በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች የተውጣጡ መሆናቸውንና የፋይናንስ ተቋማት በአክሲዮን ግዢው ላይ ገና መሳተፍ አለመጀመራቸውን የተናገሩት የቢሮ ኃላፊው፣ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ቅርንጫፎች በመላ ኦሮሚያ የአክሲዮን ሽያጩ በስኬት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመጀመሪያው ቀን የአክሲዮን ሽያጭ የተመዘገበው ውጤት ምክንያት የመንግሥትና የግል ባለሀብቶች ጥምረት ምክር ቤት ማምሻውን ተሰብስቦ በኦዳ ትራንስፖርት የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎቱን በፍጥነት እንዲጀምር፣ ለዚህ የሚያስፈልጉ ተሽከርካሪዎች ግዢ በፍጥነት እንዲፈጸም መወሰኑን አቶ ታከለ ጠቁመዋል፡፡

የኦዳ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር በሙሉ አቅሙ ሲመሠረት ከወጣቶች ጋር በጋራ የሚያስተዳድራቸው የነዳጅ ማደያዎችና የነዳጅ ዲፖዎች እንደሚኖሩት ተናግረዋል፡፡

‹‹ለሕዝብ ማሰብ ከጀመርክ ሕዝብ ካንተ ጋር መሆኑን ያየንበት ፕሮጀክት ነው፤›› በማለት አቶ ታከለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ‹‹የኢኮኖሚ አብየት›› ይፋ ከተደረገ በኋላ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሥጋታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡ የሥጋቱ መነሻ የክልሉ መንግሥት የጀመረው እንቅስቃሴ ብሔር ተኮር መሆኑ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ታከለ የተሳሳተ አመለካከት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹እዚህ አገር ላይ እንደ ኦሮሚያ ክልል የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ የለም፤›› የሚሉት አቶ ታከለ፣ ‹‹ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ መኖር ባህላችን ነው፡፡ የዚህ ምስክሩ ታዋቂው የጉዲፈቻ ሥርዓታችን ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በመሆኑም የሚወራው ከወሬነት የዘለለ አይደለም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በሕግም የተፈቀደ አይደለም፡፡ ከኦሮሞ ባህልም ያፈነገጠ አስተሳሰብ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት የሚመራው የክልሉን ሕዝብ በመሆኑ ፕሮጀክቶችን የሚያቅደው ይህንኑ ሕዝብ መሠረት አድርጎ እንደሆነ ጠቁመው፣ በኦዳ ትራንስፖርት በርካታ ኦሮሞ ያልሆኑ ባለሀብቶች አክሲዮን መግዛታቸውንና አሁንም ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹አብረን መብላትና አብረን መኖር እንችላለን፡፡ እዚህ አገር ላይ ያጣነው አብሮ መሥራት ነው፤›› የሚሉት አቶ ታከለ፣ ይህ የክልሉ መንግሥት አቋም መሆኑን አስታውቀዋል፡፡