አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 5 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከነገ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ብሄራዊ የሃዘን ቀን አወጀ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በአዲስ አበባ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በደረሰው አደጋ ህይዎታቸውን ያጡ ዜጎችን ለማሰብ ነው ከነገ ጀምሮ ብሄራዊ የሃዘን ቀን ያወጀው።
ከነገ መጋቢት 6 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው የሃዘን ቀን ለሶስት ቀናት የሚቆይ ነው።
በዚሁ መሰረት በሁሉም የሃገሪቱ ግዛቶች፣ በኢትዮጵያ መርከቦች እና በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች የሪፐብሊኩ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል።
ምክር ቤቱ በአደጋው ህይዎታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽ፥ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው የሃገሪቱ ህዝቦች መጽናናትን ተመኝቷል።
ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ቆሼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የቆሻሻ ክምር በአካባቢው ባሉ መኖሪያ ቤቶች ላይ በመናዱ ምክንያት በርካታ ዜጎች ለህልፈት ተዳርገዋል።
በተያያዘ ዜና ቅዳሜ ምሽት በደረሰው አደጋ የሟቾቹ ቁጥር 72 ደርሷል።
በዛሬው እለትም በተለያዩ የእምነት ተቋማት 9 ሰዓት ላይ በአደጋው ህይዎታቸው ያለፉ ዜጎች የቀብር ስነ ስርዓት ይፈጸማል።