Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የዳያስፖራው የባንክና የኢንሹራንስ አክሲዮኖች ለሽያጭ እየቀረቡ ነው

በባንኮችና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች ይዘው የቆዩ ከ700 በላይ የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባለድርሻዎች መገኘታቸው፣ ለብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ቀረበ፡፡ የእነዚህ ባለአክሲዮኖችን ድርሻ ለኢትዮጵያውያን በሽያጭ ለማስተላለፍ ባንኮች ጨረታ ማውጣት ጀምረዋል፡፡

ከፋይናንስ ተቋማት አክሲዮን መግዛት ለውጭ ዜጎች የተከለከለ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የውጭ ዜግነት ይዘው ባለአክሲዮን የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ ይህንን ለማጣራት በተሰጠ የጊዜ ገደብ እስካሁን ከ700 በላይ የውጭ ዜግነት የያዙ ባለአክሲዮኖች መገኘታቸውን የሚያረጋግጥ ሪፖርት፣ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ከሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ተሰብስቦ ለብሔራዊ ባንክ ሪፖርት የቀረበባቸው እነዚህ ባለአክሲዮኖች፣ በቅርቡ በወጣ መመርያ መሠረት ያላቸውን የአክሲዮን ድርሻና አክሲዮናቸው ያስገኘላቸውን ትርፍ ይዘው እንዲወጡ ዕድል ተሰጥቷቸዋል፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱ ድርሻቸውን በመስጠት የባለቤትነት ማረጋገጫ ሠርተፊኬቶቻቸውን እየተቀበሉዋቸው ነው፡፡

በአገሪቱ ሕግ መሠረት የውጭ ዜጋ ሆኖ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ መያዝ በወንጀል የሚያስጠይቅ እንደሆነ ቢታወቅም፣ በጉዳዩ ላይ ከተመከረ በኋላ የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድርሻቸውን ይዘው እንዲወጡ መወሰኑ መገለጹ አይዘነጋም፡፡ በዚህም መሠረት በግንባር ለቀረቡ ወይም በሕጋዊ ወኪሎቻቸው በኩል አክሲዮናቸውንና የትርፍ ድርሻው ይዘውት የቆዩትን ደግሞ፣ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ለማስተላለፍ የፋይናንስ ተቋማቱ ግልጽ ጨረታ እያወጡ ነው፡፡

የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለአክሲዮኖችን ድርሻ ለጨረታ እያቀረቡ ያሉትም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቁጥር FIS/01/2016 ባስተላለፈው መመርያ መሠረት ነው፡፡

በባንኮችና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች የውጭ ዜግነት ባላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስም የተመዘገቡ አክሲዮኖችና የአክሲዮን ሠርቲፊኬቶች ለኩባንያዎቹ ተመልሰው፣ አክሲዮኖቹን በገዙበት ዋጋ ለባለድርሻዎቹ እንዲከፈል ተወስኗል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ እስካሁን የውጭ ዜግነት ያላቸው ተብለው የተለዩት 710 ናቸው፡፡ የባለአክሲዮኖች ድርሻም ከ0.8 እስከ 1.0 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡

በባለቤትነት ይዘዋቸው የነበሩ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ክፍያ የፈጸሙባቸውን አክሲዮኖች በግልጽ ጨረታ እንዲሸጡ የሚገደዱ በመሆናቸው፣ የአክሲዮኖቹን ሽያጭ ለመፈጸም ባንኮች የጨረታ ማስታወቂያዎቹን ማውጣት ግድ ብሏቸዋል፡፡ ጨረታው ከዚህ ቀደም ለባለአክሲዮኖች ቅድሚያ ይሰጥ የሚለውን ወደ ጎን በማለት፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው በሙሉ የሚሳተፉበት ነው፡፡ አንዳንድ ባንኮች የአክሲዮን ሽያጫቸውን ከባለአክሲዮኖች ውጪ ለመሸጥ የሚያስችላቸው የመተዳደሪያ ደንብ ባይኖራቸውም፣ የውጭ ዜግነት ባላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተያዙ አክሲዮኖችን ለመሸጥ የውስጥ መተዳደሪያ ደንባቸውን እስከመቀየር ሊያደርሳቸው እንደሚችል የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ለጨረታ የሚቀርቡት አክሲዮኖች የሚያስገኙት ትርፍ በቀጥታ ለመንግሥት ገቢ ይደረጋል፡፡ ዋናው የአክሲዮን ዋጋ ደግሞ ባንኮች ለተሰናባቾቹ ባለአክሲዮኖች ቀድመው ክፍያ የፈጸሙ በመሆናቸው ለባንኮቹ ተመላሽ ይደረጋል፡፡ እስካሁን ቀርበው ያልወሰዱም ካሉ በመጡ ጊዜ የአክሲዮን ድርሻቸውን መውሰድ እንደሚችሉም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 34 የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በድምሩ ከ140 ሺሕ በላይ አክሲዮኖቻቸው የውጭ ዜግነት ባላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተይዘው ነበር፡፡ ኩባንያዎቹ በአሁኑ ወቅት ከ46 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ በመሆናቸው፣ እስካሁን ሪፖርት በተደረገው መሠረት የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለአክሲዮኖች ድርሻ ከ350 እስከ 400 ሚሊዮን ብር ዋጋ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡
Source: Ethiopian reporter