Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ከምዕራባዊ ትግራይ ዞን ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 14 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በድንበር አካባቢ የሚገኙ የምዕራብ ትግራይ ነዋሪዎች የአካባቢውን ልማት በማረጋገጥና ሰላምን በመጠበቅ እያደረጉ ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው እለት ከዞኑ ነዋሪዎች ጋር በሁመራ ከተማ ውይይት አካሂደዋል።

ነዋሪዎች ዞኑን ከወረዳና ከሱዳን ጋር የሚያገናኙ መንገዶች እና የጤና ተቋማት ግንባታ ሊከናወን ይገባል በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

በዞኑ የተገነባው የከብት ማድለቢያ ኳራንቲንም ስራ የሚጀምርበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በህዝቦች መካከል መቃቃርን ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች ላይ መንግስት እርምጃ ይውሰድ ሲሉም ሃሳብ ሰንዝረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው መንግስት በሽብር ቡድኖች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ በመጥቀስ፥ ዞኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ያገኛል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዞኑ ነዋሪዎች የተበረከተላቸውን ኩታ ደርበው

በህዝቡ የተነሱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በአፋጣኝ ምላሽ ያገኛሉም ነው ያሉት፤ ያለ አገልግሎት የተቀመጠው ኳራንቲን ጉዳይ በባለሙያ ተፈትሾ ምላሽ እንደሚያገኝ በመጠቆም።

የዞኑ ነዋሪዎችም በዞኑ የልማት እንቅስቃሴዎችን በማስቀጠል በድንበር አካባቢ ሰላምን ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ህዝቡ በትግሉ ወቅት ያሳየውን ተጋድሎም በድህነት ላይ ሊደግመው ይገባልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በነዋሪዎቹ የተነሱ ጥያቄዎችና ሃሳቦችም በአፋጣኝ ምላሽ እንደሚያገኙ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መንግስት የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ የተጠናከረ ተግባር እንደሚያከናውንም አንስተዋል።