Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴው ውጤታማ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ


አዲስ አበባ ጥር 1/2009 በአሁኑ ወቅት እስከታች የዘለቀው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።

የዴሞክራሲ ተሳትፎን ለማጎልበት ኢሕአዴግ “ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋር ድርድርና ውይይት ለማድረግ ዝግጁ ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዛሬ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በአገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“በጥልቅ ተሃድሶው የአመራር ሥርዓቱ ለአገልግሎት የተዘጋጀ ከሆነ ሂደቱን በሚገባ ማሻሻል ይቻላል” የሚል እምነት ተይዞ እንደተገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

በዚህም አገልጋይ ለመፍጠር የተደረገው ጥረት ራሱን የሰጠ አመራር አባል መፍጠር የተቻለ ሲሆን፤ “የእስካሁኑ ቁርጠኛነታቸውም ይህንኑ የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

በፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነትና በመልካም አስተዳደር ትግሉም ህዝቡን ለማሳተፍ የተደረገው ጥረት ስኬታማ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሕዝቡም የሚያገለግለውን የአመራር አባል በነቃ ተሳትፎ መምረጡም የተሃድሶው ስኬት ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

የተሃድሶው እንቅስቃ ኅብረተሰባዊ መሆን እንደጀመርም አመልክተዋል።

ከመንግሥትና ከድርጅት ባለፈ “የመንግሥት ሠራተኛው የለውጡ አካል ተደርጎ የአገልጋይነት ባህልን ለማዳበር በተሃድሶው እንዲታቀፍ ይደረጋል” ነው ያሉት።

ይህም በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲቃለልና ሠራተኛው ነፃ ሆኖ እንዲሳተፍ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

ሲቪል ሰርቪሱ ሕዝቡን በቅንነት የማገልገል ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችል እንደሆነ ጠቁመው፤ ሆኖም የማያላውስ ነገር ውስጥ የገቡ ሠራተኞች ግን ከሥርዓቱ ማስወጣት ግድ እንደሚል ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመለከቱት።

“በኅብረተሰቡ ውስጥ የመታደስ አስተሳሰብ ሊኖር ይገባል” ያሉት አቶ ኃይለማርያም፤ ድምር ውጤቱ አገራዊ ለውጥ የሚያስገኝ መሆኑን ነው በአጽንኦት የገለጹት።

ሕዝባዊ ንቅናቄው በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም ወጣቱን በተሃድሶ እንቅስቃሴ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆነበት አሰራር የተዘረጋ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአኳያው ወጣቱ ሥራን ሳይንቅ የመስራት ባህሉን ሊያጎለብት እንደሚገባም ተናግረዋል።

በንግዱ ኅብረተሰብ በኩልም ንቅናቄ በመፍጠር በሕገ-ወጥ መንገድ ለመክበር የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጭምር ፈተና ውስጥ የሚከቱትን በዝምታ እንደማይታለፉ ግልጽ አድርገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዴሞክራሲ ተሳትፎን ለማጎልበትና የተሟሟቀ የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማድረግ “ኢሕአዴግና መንግሥት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በቅርቡ ድርድርና ውይይት ያካሂዳሉ” ብለዋል።

ድርድሩ ታዳጊ የሆነው አገራዊ የዴሞክራሲ ተሳትፎን ከማጎልበት አኳያ የሚታይ ሲሆን፤ በእንቅስቃሴውም የመገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪክ ማኅበራትና የሕዝብ አደረጃጀቶች እንደሚታቀፉ አመልክተዋል።

ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ድርድርም የዚህ አንድ ክፍል ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፓርቲዎቹ ጋር የሚደረጉ ድርድሮችን የሚከታተል ማዕከል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መቋቋሙን ተናግረዋል።

በኢሕአዴግ በኩል ለድርድሩ ዕቅድ ወጥቶ ዝግጁት መደረጉን ገልጸው፤ ለድርድሩ በግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቁመዋል።

በድርድሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የኢሕአዴግን ፖሊሲ ከማብጠልጠል ባለፈ አማራጭ ፖሊሲያቸውን ለሕዝቡ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ የሚገባውን ልዩ ጥቅም ለማግኘት በሕገ-መንግሥቱ በግልጽ እንደተቀመጠው ሕግ እንደሚወጣለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም ረቂቅ ሕግ የተዘጋጀ ሲሆን በአመራር አባላት ደረጃ ታይቶ ሕዝቡ የሚወያይበት ሲሆን፤ “የሕግ አፈፃጸምን ተከትሎ ተግባራዊ ይደረጋል” ብለዋል።

One Response to የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴው ውጤታማ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ