አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የተለዋጭ አባልነት ስፍራዋን ዛሬ በይፋ ተረክባለች።
ከኢትዮጵያ ጋር በተለዋጭ አባልነት የተመረጡት ጣሊያን፣ ካዛኪስታን፣ ስዊድን እና ቦሊቪያም በዛሬው እለት አባልነታቸውን በይፋ ጀምረዋል።
ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ዓመታት የምታገለግል ይሆናል።
አገሪቱ በሚኖራት ቆይታም የዓለም ደህንነትና ሠላምን ለማረጋገጥ፣ ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለማስወገድ ከሌሎች የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት ጋር እንደምትሰራ ማስታወቋ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በተደረገው ምርጫ ነው አፍሪካን በመወከል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆና የተመረጠችው።
በወቅቱ በተደረገው ምርጫም ድምፃቸውን ከሰጡ 190 ሀገራት መካከል የ185 የድርጅቱ አባል አገራትን ድምፅ በማግኘትም መመረጧም ይታወሳል።
በዛሬው እለት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት ስፍራቸውን የተቀበሉት አምስቱ ሀገራት የቆይታ ጊዜያቸው ትናንት ያጠናቀቁትን አንጎላ፣ ማሌዥያ፣ ኒው ዚላንድ፣ ስፔን እና ቬንዙዌላ ተክተው ለሁለት ዓመታት የሚያገለግሉ ይሆናል።
ጣሊያን እና ኔዘርላንድስ ግን በምርጫው ወቅት እኩል 95 ድምጽ ማግኘታቸውን ተከትሎ የሁለት ዓመት ቆይታውን ለመካፈል መስማማታቸው ይታወሳል።
በዚህም መረሰት ጣሊያን በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት ስፍራ ላይ በቅድሚያ ለ1 ዓመት የምታገለገል ሲሆን፥ ኔዘርላንድስ ደግሞ በቀጣዩ የፈረንጆቹ 2018 ለ1 ዓመት የተለዋጭ አባልነቱን ከጣሊያን ትረከባለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 9ኛ ዋና ፀሃፊ በመሆን የተመረጡት ፖርቹጋላዊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝም በዛሬው እለት በይፋ ስራቸውን ጀምረዋል።
ዋና ፀሓፊው በአውሮፓውያን አዲሱ የ2017 የመጀመሪያው ቀን በተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት ተገኝተው አዲሱ ዓመት ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን ለመሥራት ቃል ገብተዋል።
የፀጥታው ምክር ቤት አባልነት ምን ጥቅሞችን ያስገኛል?
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባል መሆን በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይነገራል።
ከእነዚህም ውስጥ ሀገሪቱ በዓለም ሀገራት ላይ ያላት ተደማጭነት እንዲጨምር ያደርጋል።
በየትኛውም ዓለም በሚኖር ግጭት ሀገሪቱ የራሷን አቋም እንድትይዝ፣ በአፍሪካ ላይ ያላት የመሪነት ሚናም እንዲጨምር እና ብሄራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጠቀሜታዎችም አሉት።
በአዲስ አባበ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰር ደመቀ አጢሶ፥ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባልነት ቀጥታ እና ቀጥታ ባልሆነ መንገድ የሚገኙ ጠቀሜታዎች አሉት ይላሉ።
ቀጥተኛ ጥቅሞቹም ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ስፍራ እና ከበሬታ ከፍ እንዲል ማድረግ እና ከአደጉ ሀገራት ጋር አብሮ የመስራት እድልን መፍጠር ነው ብለዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ከአገራቱ የምታገኘው ድጋፍ ከፍ እንዲል ያደርጋል ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰር ደመቀ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ቀጥተኛ ባልሆነ ጠቀሜታ የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ ተሰሚነት ከፍ እንዲል እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ የምክር ቤቱ አባል ሆና አገልግላለች።
የአሁኑ አባልነቷ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን፥ ይህም ከዚህ በፊቶቹ በበርካታ መልኩ እንደሚለይ ረዳት ፕሮፌሰር ደመቀ ይናገራሉ።
ይህም ሀገሪቱ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት እያበረከተችው ያለው አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ እንዲገባ በማድረግ በሀገሪቱ አንጻራዊ ሰላም እንዳለ የሚያሳይ በመሆኑ፥ የሀገሪቱ የውጭ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል።
የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት 15 አባል ሀገራት ያሉት ሲሆን፥ ከነዚህም ውስጥ አምስቱ ሀገራት ቋሚ፤ 10 ሀገራት ደግሞ በየሁለት ዓመቱ የሚመረጡ ተለዋጭ አባል ናቸው።
የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል ሀገራትም አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና ሩሲያ ሲሆኑ፥ በዛሬው እለት የተቀላለቁለትን አምስት ሀገራት ጨምሮ ግብፅ፣ ሴኔጋል፣ ዩክሬን፣ ኡራጉዋይ እና ጃፓን በተለዋጭ አባልነት ያገለግላሉ።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1967 እስከ 1968 እንዲሁም ከ1989 እስከ 1990 ለሁለት ያህል ጊዜ ማገልገሏ ይታወሳል።
በሙለታ መንገሻ