አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ።
ሊንዳ ቶማስ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ይመክራሉ።
ረዳት ሚኒስትሯ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ባለስልጣናት እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ሰራተኞች ጋር እንደሚነጋገሩም ነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በዛሬው እለትም ወደ ደቡብ ሱዳን ጁባ እንደሚያመሩ እና በሀገሪቱ ከሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ ተጠቁሟል።
በደቡብ ሱዳን ሰብአዊ ድጋፍ እያደረጉ ከሚገኙ አለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች እና ጋዜጠኞች ጋር የሚነጋገሩ ይሆናል ተብሏል።
የአሜሪካ እና ደቡብ ሱዳን የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮችም ላይ ከሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ ።