አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተጓተቱ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶችን መንስኤ የሚጠቁም እና ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለመለየት የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ነው።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርቱን ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።
ኮሚቴውም በስኳር እና በማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ላይ የታየው ከልክ ያለፈ መጓተት ምክንያት እና ተጠያቂ አካላት እንዲቀርቡ አሳስቧል።
ከመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ጋር በተያያዘ ወጥነት ያለው አፈፃፀም አለመታየቱ ተነስቷል።
ፕሮጀክቶቹ ሲቀረፁ የአዋጭነት ጥናት አለመደረግ፣ የቦታ መረጣ ችግር እና በቂ ፋይናንስ ሳይኖር ወደ ስራ መግባት ለመዘግየቶቹ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
ከኮሚቴው አባላት በተለይ ከስኳር እና ማዳበሪያ ፋብሪካዎች አፈፃፀም ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በሰጡት ምላሽም፥ የስኳር ኮርፖሬሽን እና ፕሮጀክቱን የወሰደው ተቋራጭ ተቀራርበው መስራት ሲገባቸው በአጭር ጊዜ ክፍያ መፈፀም ሲገባ እስከ ሁለት አመት የቆየ የክፍያ ስርአት እንዳለ ገልፀዋል።
ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት ተጠያቂው ኮርፖሬሽኑ ነው ወይንስ ተቋራጮች ናቸው የሚለውም በጥናት የመለየት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ጥናቱ በቅርቡ ሲጠናቀቅ ጥፋተኛ ሆኖ በተገኘው አካል ላይ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
መንግስት ከልማት ድርጅቶች ማግኘት የሚገባውን ትርፍ እያገኘ አይደለም የሚለውም ከኮሚቴው አባላት ተነስቷል።
በተለይ አንዳንድ ተቋማት የስራ ማስኬጃ ካፒታላቸው አነስተኛ በመሆኑ የትርፍ ክፍፍሉን በተገቢው ወቅት ለመንግስት ገቢ ያለማስገባት ችግር እንደሚታይባቸው ተገልጿል።
በቀጣይም ጉዳዩን ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በመውሰድ የስራ ካፒታላቸው ከፍ እንዲል ለማድረግ እና የተሻለ ምርታማ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ይከናወናል ተብሏል።
አንዳንድ ተቋማት ለረጅም ጊዜ ሂሳባቸው ኦዲት ሳይደረግ እየተንከባለለ መምጣት ለመልካም አስተዳደር እና ብልሹ አሰራሮች በር ከመክፈቱ ጋር ተያይዞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኦዲት መደረግ የሚገባቸውን ተቋማት ሂሳባቸውን እንዲሰራ ተጠይቋል።