Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ሀይማኖታዊ መንግስት ለማቋቋም የተንቀሳቀሱ 20 ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ


አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአክራሪነት አስተሳሰብና አስተምህሮ በመያዝ በሀገሪቱ ውስጥ ሌላ የእምነት አስተሳሰብና አስተምህሮ መኖር የለበትም በማለትና ሀይማኖታዊ መንግስት ለማቋቋም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 20 ግለሰቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ።

በእነ ከድር መሀመድ መዝገብ በአቃቤ ህግ የተመሰረተባቸውን ክስ ሲከታተሉ የቆዩት ተጠርጣሪዎቹ፥ ታህሳስ 12 ቀን 2009 ዓ.ም የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው ሲሆን በዛሬው እለትም የእስር ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

ተከሳሾቹ 1ኛ ከድር መሀመድ፣ 2ኛ ነዚፍ ተማም እንዲሁም 3ኛ ፉዓድ አብድል ቃድርና ሌሎች በመዝገቡ የተጠቀሱ 17 ግለሰቦች ናቸው።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን፣ የወንጀል አድማ ስምምነት በማድረግ፣ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት የተረጋገጡትን ነጻነቶች በመቃረን እንዲሁም በሀገሪቱ ሌላ አስተሳሰብና ሀይማኖታዊ አስተምህሮ መኖር የለበትም የሚል አላማ በመያዝ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

በተጨማሪም ሀይማኖታዊ መንግስት በሀገሪቱ ለማቋቋምና በመንግስት ላይ ጫና በማሳደር “ድምጻችን ይሰማ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” አባላትን ከእስር ለማስፈታት መንቀሳቀሳቸውም በክሱ ተገልጿል።

ተከሳሾቹ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ መስጊዶች ህዝብን የሚያነሳሱ በራሪ ወረቀቶችን በመበተን እና በጅማና በወልቂጤ ደግሞ አመጽ ለማስነሳት ተንቀሳቅሰዋል የሚለውም በጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ ላይ ተብራርቷል።

በተለይም 1ኛ ተከሳሽ ከድር መሀመድ መንግስትን ከስልጣን አውርዶ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት የሽብር እንቅስቃሴ በመላው ሀገሪቱ በማካሄድ በሸሪያ ህግ የሚመራ እስላማዊ መንግስት በኢትዮጵያ መመስረት አለበት በሚል መንቀሳቀሱ በክስ መዝገቡ ተጠቅሷል።

ተከሳሹ ይህን አላማውን ለማሳካትም አቃቤ ህግ የጅማ አመጽን ሲመሩ ነበሩ ያላቸውን ነዚፍ ተማም እና ሀሮን ሀይረዲንን እንዲሁም የሹራ አባል አመራር ነበር የተባለውን ፉዓድ አብድልቃድር ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ በማድረግ አመጹን ለማስፋፋት መንቀሳቀሱም በክሱ ተብራርቷል።

የተቀሩት ተከሳሾችም በአመጽ ሰልፎችና በራሪ ወረቀቶችን በመበተን እንዲሁም በማስተባበራቸው ነው በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይነት ክስ የተመሰረተባቸው።

አቃቤ ህግ ጉዳዩን ለመረመረው የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ የወንጀል ችሎት ክሱን ያጠናክርልኛል ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ አሰምቷል።

ተከሳሾቹም በአቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ማስረጃዎች ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

በአቃቤ ህግ በኩል የቀረበ የቅጣት ማክበጃ የለም፤ ነገር ግን በተከሳሾቹ በኩል ከቀረቡት የቅጣት አስተያየቶች ውስጥ ሁለቱን ፍርድ ቤቱ ይዞላቸዋል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛው የወንጀል ችሎት ከ13ኛ ተከሳሽ በቀር ሁሉንም በ5 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

13ኛ ተከሳሽ በህመም ላይ የሚገኝ በመሆኑ ሶስተኛ የቅጣት ማቅለያ አድርጎ በመያዝ በ4 ዓመት ከ5 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል።

በሰለሞን ጥበበስላሴ