ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ ስምምነት ከሶስተኛ ወገን ጋር እንደማታደርግ አስታወቀች
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ ማንኛውንም ስምምነት ከሶስተኛ ወገን ጋር እንደማታደርግ የሀገሪቱ አምባሳደር አስታውቀዋል።
መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉት የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒቲያም ኦርጋን ለኢቢሲ እንደተናገሩት፥ ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ጥቅም የሚፃረር ስምምነት እንደተፈራረመች የተባለው እውነት አይደለም ብለዋል።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር መያርዲት ከቀናት በፊት በግብጽ ጉብኝት ማድረጋቸውን ያስታወሱት አምባሳደሩ፥ የጉብኝቱ አላማም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በተቃረኒ መልኩ በአንዳንድ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ጥቅም የሚፃረር ስምምነት እንደተፈራረመች ተደርጎ እየተሰራጨ ያለው አሉባልታ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል።
አገራቸው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ ማንኛውንም ስምምነት ከሶስተኛ ወገን ጋር እንደማታደርግም አምባሳደሩ አስታውቀዋል።
አምባሳደሩ አያይዘውም ደቡብ ሱዳን ተጨማሪ የሰላም አስከባሪ ሀይል ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ተጨማሪ 4 ሺህ ሰላም አስከባሪ ሃይል መስፈር እንዳለበት ከውሳኔ መድረሱ ይታወሳል።
ውሳኔውን ተከትሎ ደቡብ ሱዳን ተጨማሪ ሃይል ወደ ሃገሯ እንዳይገባ ስትቃወም ቆይታለች መባሉን መቀመጫቸውን በአዲስ አበበ ያደረጉት የሃገሪቷ አምባሳደር አስተባብለዋል።
በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ልኡክ ከደቡብ ሱዳን ካቢኔ ጉዳዮች ሚንስትር ማርቲን ሉዋሮ ጋር ባደረገው መክክርም ሀገሪቱ ተጨማሪ የሰላም አስከባሪ ሀይል ለመቀበል መዘጋጀቷን አምባሳደሩ ጀምስ ፒቲያም ኦርጋን ተናግረዋል።
መንግስታቸው በኢጋድ አደራዳሪነት ለተፈረመው ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት እየሰራ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ ፥ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት እያደረገች ያለውን ጉልህ ሚናም አድንቀዋል።