Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የመቀሌ ከተማን የውሃ አቅርቦት ችግር ለማቃለል የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል – አቶ አባይ ወልዱ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመቀሌ ከተማ የሚታየውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለማቃለል በሚቀጥሉት ሶስት ወራት የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል አሉ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አባይ ወልዱ።

ርዕስ መስተዳደሩ የገረብ ሰገን ግድብ ግንባታንና የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ትናንት ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የክልሉ የውሀ ግንባታ ስራዎች ኢንተርፕራይዝ ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረመድህን ተስፋዬ ፥ ከ33 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው የገረብ ሰገን ግድብ ግንባታ በ2006 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ግንባታው በአብዛኛው ተጠናቆ በቂ ውሀ ማከማቸቱን የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ፥ ከግድቡ በታች የሚሰሩ የውሀ ማከሚያዎች፣ የመስመር ዝርጋታና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎች በሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የውሀ ማጠሪያና የውሀ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ከአውሮፓና ከቻይና የሚመጡ በመሆናቸው አቅራቢዎች በወቅቱ ባለማድረሳቸው እንዲሁም በየጊዜው የዲዛይን መቀያየር ምክንያት ግንባታውን እንዳጓተተውም ነው ያብራሩት።

ለግድቡ ግንባታ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት የጠቆሙት አቶ ገብረመድህን፥ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በመጀመሪያው ምዕራፍ በዓመት ከ7 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሜትር ኪዩብ ውሀ ለከተማው ማቅረብ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለመጠጥ ውሃ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮችንም ተጠቃሚ የሚያደርግ 600 ሄክታር መሬት በመስኖ የሚያለማ መሆኑን አንስተዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ አባይ ወልዱ በበኩላቸው እቃ ለማቅረብ ጨረታ ያሸነፉ አቅራቢዎች በገቡት ውል መሰረት እንዲፈጽሙ ክትትል በማድረግ ቀሪ ስራዎች እንዲጠናቀቁ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪም በመቀሌ ከተማ አካባቢ በመገንባት ላይ ያለውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ሲጎበኙ የፓርኩ ፕሮጀክት ተጠሪ አቶ ዘካሪያስ ገብረአነኒያ፥ የፓርኩን ግንባታ እስከ የካቲት 20 2009 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ ተቋራጩ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኩ ከሚገነቡ 15 ሼዶች ውስጥ ስድስቱ ጣራቸው መልበሱን ጠቁመው ቀሪዎቹ ደግሞ በተለያዩ የግንባታ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር መገለጹንም ነው የኢዜአ ዘገባ ያመለከተው።