አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በአገር ውስጥ ዕውቅና ካገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመከራከርና ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ገለጸ።
ድርጅቱ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርገው ክርክርና ድርድር በቀጣዩ ሣምንት መካሄድ እንደሚጀምር አስታውቋል።
የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የድርጅቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፥ ድርጅቱ እንደ ገዢ ፓርቲ በጋራ ከመስራት አኳያ የነበረበትን ውስጣዊ ክፍተት በመለየት በአገራዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ይበልጥ ተቀራርቦ ለመስራት ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ቀደም ሲልም አብሮ ለመስራት ፍላጎቱ ካላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የጋራ ምክር ቤት መስርቶ ሲሰራ መቆየቱንም አንስተዋል።
ሰላማዊ እስከሆኑ ድረስ ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ማናቸውም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል።
ሃላፊው እንዳብራሩት፥ ኢህአዴግ በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ውይይትና ድርድር ያደርጋል፤ በሚለያዩባቸው ጉዳዮች ደግሞ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር ክርክር ያካሂል።
በዚህም ፓርቲዎቹ ለሕዝቡ “አለን” የሚሉትን ሀሳብ አቅርበው ህዝቡ አጀንዳቸውን በግልጽ እንዲያይና እንዲወስን የሚያስችለውን ግንዛቤ ይይዛል ነው ያሉት።
ኢህአዴግ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ያቀረበው ግብዣ አዲስ እንዳልሆነ አቶ ሽፈራው ጠቅሰው፥ ደርግን አሸንፎ በመሰረተው የሽግግር መንግሥት ሁሉም ፓርቲዎች ተሳትፎ እንዲኖራቸው መጋበዙን በማሳያነት አንስተዋል።
ሕገ-መንግሥቱን በማርቀቅና በማጽደቅ በኩል የነበረው ተሳትፎም አቶ ሽፈራው በማሳያነት ያቀረቡት ሌላው ጉዳይ ነው።
የአሁኑን የተለየ የሚያደርገው ሠላማዊ እስከሆኑ ድረስ ‘መመሪያውን ፈረሙ አልፈረሙ’ የሚል ድንበር አይበጅላቸውም ነው ያሉት።
ኢህአዴግም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ የድርድር ሥርዓቱ ምን ሊሆን እንደሚችል የየራሳቸውን ሃሳብ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ጉዳይ ፍላጎት ያላቸው ኢህአዴግን ጨምሮ ፓርቲዎች ብቻ እንዳልሆኑ ግን ግንዛቤ ሊያዝ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የተለያዩ የኅብረሰተብ ክፍሎች፣ ምሁራንና የሲቪክ ማኅበራት መኖራቸውን ገልጸው ኢህአዴግ ከእነዚህም ጋር በአጋርነት መስራት እንደሚፈልግ ይፋ አድርገዋል።
የፖለቲካ አቋምና ክርክር ሳይሆን በአማካሪነት፣ አዳዲስ ሃሳቦችን በማመንጨትም ይሁን ክፍተቶችን በማመላከት አሊያም ህዝብና አገርን በመወከል በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ይሁን በምርምር ሥራ አብሮ መስራትን ያካትታል።
የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴም ይህንኑ ጉዳይ በቅርቡ ግልጽ አድርጓል።
የዴሞክራሲ ተሳትፎን ለማጎልበትና የተሟሟቀ የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማድረግ ኢህአዴግና መንግሥት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በቅርቡ ድርድርና ውይይት እንደሚያካሂዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሳምንቱ መግቢያ መናጋራቸው ይታወሳል።
ድርድሩ ታዳጊ የሆነውን አገራዊ የዴሞክራሲ ተሳትፎ ከማጎልበት አኳያ የሚታይ ሲሆን፥ በእንቅስቃሴውም የመገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪክ ማኅበራትና የሕዝብ አደረጃጀቶች እንደሚታቀፉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ከፓርቲዎቹ ጋር የሚደረጉ ድርድሮችን የሚከታተል ማዕከል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንደተቋቋመም ተናግረዋል።
በኢህአዴግ በኩል ለድርድሩ ዕቅድ ወጥቶ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፥ ለድርድሩ በግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር የሚመራ ኮሚቴ እንደተቋቋመ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
በአገር አቀፍ ደረጃ በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያላቸው 23 ፓርቲዎች በውይይቱ ተካፋይ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።