Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የወልዲያ-ሓራ-መቀሌ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት በአንድ ዓመት ይጠናቀቃል

ታህሳስ 1፣2009

በአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በጀት ግንባታው እየተፋጠነ ያለው የወልዲያ-ሓራ-መቀሌ 316 ኪሎ ሜትር የባቡር መንገድ ፕሮጀክት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ።
woldia-mekele
ግንባታው በ2007 ዓ.ም የተጀመረው የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ግንባታው እየተካሄደ ያለው በቻይናው የኮሚኒኬሽንና ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (ሲሲሲሲ) አማካኝነት ነው።

በፕሮጀክቱ ግንባታቸው በመካሄድ ላይ ከሚገኙት ስምንት የዋሻ ውስጥ የባቡር መንገዶች መካከል የአንድ ነጥብ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአሮሌ ቁጥር አንድ ዋሻ ቁፋሮ ሥራ ሰሞኑን ተጠናቅቋል።

በዋሻው ቁፋሮ ማጠናቀቂያ ስነ ስርዓት ላይ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ገብረመድህን ገብረአሊፍ እንደገለጹት፣ በአፋር ክልል ዞን ሁለት ኮኮሌ በተባለው አካባቢ የሚገኘው የዋሻ ውስጥ ባቡር መንገድ ቁፋሮ የተከናወነው ከሁለት የተለያየ አቅጣጫ በመነሳት መሃል ላይ በማገናኘት ነው።

ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፣ በፕሮጅክቱ ከሚገነቡት የዋሻ ውስጥ የባቡር መንገዶች መካከል በትልቅነቱ ሦስተኛ የሆነው የአሮሌ ዋሻ ቁፋሮ የተከናወነው በሁለት ከፍተኛ አለት ሰርሳሪ መሳሪያዎች አማካኝነት ነው።

የዋሻው መንገድ የቁፋሮ ሥራ ሁለት ዓመት የሚጠጋ ጊዜ መፍጀቱን ኢንጂነር ገብረመድህን አስታውቀዋል።

በፕሮጀክቱ የሚገነቡት ስምንት የዋሻ ባቡር መንገዶች 10 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳላቸው አስታውሰው፣ “በትልቅነቱ ቀዳሚ የሆነውን የሦስት ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር የዋሻ ባቡር መንገድ ቁፋሮ በቅርቡ ይጠናቀቃል” ብለዋል።

የወልድያ – ሓራ – መቀሌ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ በመፋጠን ላይ እንደሚገኝና በሚቀጥለው ዓመት የካቲት ወር ላይ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ለፕሮጀክቱ ግንባታ የአርማታ ማቀናባበሪያና የድልድይ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ገልባጭ መኪኖች፣ ግሬደሮች፣ ዶዘሮችና ስካቫተሮች በተደራጀ መልኩ ሥራ ላይ ውለዋል።

ኢንጂነር ገብረመድህን እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ከ42 ነጥብ ሰባት በመቶ በላይ ደርሷል።

“አሁን ባለበት ደረጃ ከ60 በመቶ በላይ የአፈር ጠረጋ፣ ድልዳሎና ጠጠር ማንጠፍ ሥራዎች ተጠናቀዋል” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ለመንገዱ የተጀመሩት 75 ከፍተኛ ድልድዮችና 270 የውሃ ማስተላለፊያ ካልበርቶች ግንባታቸው ከ42 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ አንዳንድ ፈታኝ ሁኔታዎች ከማጋጠማቸው በስተቀር አብዛኛው የፕሮጀክቱ ግንባታ በጥሩ ሁኔታና በተያዘለት የጊዜ ገደብ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ በቻይናው የኮሚኒኬሽንና ኮንስትራክሽን ካምፓኒ የወልድያ – ሓራ – መቀሌ ባቡር መንገድ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ጋኦ ጁን ሆንግ በበኩላቸው፣ የአካባቢው መልካዓ ምድር አቀማመጥና በረሃማ የአየር ንብረት በአሮሌ ቁጥር አንድ ዋሻ ግንባታ ላይ የተወሰነ ተፅዕኖ ቢያደርስም ችግሩን በመጋፈጥ የዋሻውን ቁፋሮ በ23 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል።

ለውጤቱ በፕሮጀክቱ ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያንና ቻይናውያን ሠራተኞችና ባለሙያዎች የተቀናጀ ጥረት የጎላ እንደነበር አስታውሰዋል።

ፕሮጀክቱ የሥራ ዕድል ከፈጠረላቸው መካከል ወጣት ቴዎድሮስ አሰፋ በሰጠው አስተያየት፣ በፕሮጀክቱ ከተቀጠረበት ጊዜ አንስቶ ጥሩ ደመወዝ በማግኘት ተጠቃሚ ከመሆኑ በተጨማሪ በባቡር መንገድ ግንባታ ዘርፍ ሙያ መቅሰሙና ለሀገሩ ልማት አስተዋጽኦ ማድረጉ እንዳስደሰተው ተናግሯል።

የባቡር መንገድ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተቀጥሮ እያገለገለና በእዚህም ተጠቃሚ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት ፋኑስ ገብረጻድቅ ነው።

በአሁኑ ወቅት በባቡር ግንባታ ፕሮጀክቱ ከአምስት ሺህ በላይ ሰዎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡