Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ቴክኖ ፓርክ ማዕከል ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ ታህሳስ 19/2009 የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ቴክኖ ፓርክ ማዕከል በ28 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሊገነባ ነው።

የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የማዕከሉን የአዋጪነት ጥናት ካቀረበው የኮሪያ ግየንግቡክ ቴክኖ ፓርክ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር ተወያይቷል።

ማዕከሉ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ጥናትና ምርምር፣ የምርት ልማት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የትምህርትና ስልጠና፣ የፖሊሲ ቀረፃ፣ የቢዝነስ ማበልፀጊያና የገበያ ጥናት አገልግሎት ይሰጣል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቦጋለ ፈለቀ ማዕከሉ የአገሪቷን የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች የጥራትና የብቃት ክፍተት በመሙላት ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ከሁለት ወር በኃላ የሚጀመረው የማዕከሉ ግንባታ በሁለት ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርና በቀጣይ ለሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሞዴል እንደሚሆንም ገልጸዋል።

የኮሪያ መንግስት ማዕከሉን በአሰልጣኞች፣ በባለሙያዎችና በማሽነሪ የተሟላ ለማድረግ ለሚያደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

የኮሪያ ግየንግ ቴክኖ-ፓርክ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር ጃኢሆን ርሄ በበኩላቸው የማዕከሉ መገንባት አገራቸው በዘርፉ ያላትን የቴክኖሎጂና የዕውቀት ልምድ ማካፈል እንደሚያስችላት ተናግረዋል።

ማዕከሉ የኢትዮጵያን የጨርቃጨርቅ ምርት በዓለም ዓቀፍ ገበያ በጥራትና በመጠን ተወዳዳሪ ለማድረግ እንደሚያግዝም ነው የገለጹት።

ለማዕከሉ የሲቪል ግንባታ የሚያስፈልገው 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ፣ ቀሪው ደግሞ በኮሪያ መንግስት የሚሸፈን ይሆናል።