Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ኣምና በዚች ቀን በታሪክ ማህደር የተመዘገበ ክህደት : ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ

alpha-negari-logo
ኣምና በዚች ቀን በታሪክ ማህደር የተመዘገበ ክህደት

ኣምና በዚች ቀን ማለትም ህዳር 29 ቀን 2008 ዓ/ም በመተማ ወረዳ ልዩ ስሙ ሽንፋ በተባለ ትንሽ ከተማ የብሄር ብሄረስቦች በዓል ለማክበር በጣም ብዙ ህዝብ ተሰበሰበ። በኣሉን ለማድመቅ በሚመስል ከ20 ሺ በላይ ከመላው የኣማራ ክልል የተወጣጣ ነው የተባለው ታጣቂ ምልሻ በኣይሱዙ ተጭኖ “ይለያል ዘንድሮ” እያለ በጭኸት እየፎከረ ሽንፋ ላይ ተሰበሰበ። የኣካባቢው የረጅም ጊዜ ነዋሪ የሆኑትን የትግራይ ብሄር ተወላጆችም ኣገር ሰላም ነው ብለው በቦታው ተገኙ። በዚህ ወቅት ነበር በዓሉን ለማክበር የሄዱት የትግራይ ተወላጆችን በመለየት “ይህ በዓል ስለማይመለከታችሁ ከሰልፉ ውጡ” በማለት በታጣቂዎች ተነድተው ከሰልፉ የተባረሩት። በዚህ ኣላበቃም ሰልፉ ሲያልቅም ከሺ ኣምስት መቶ ታጣቂዎች በላይ በከተማውና ኣካባቢውን እየዞሩ የትግራይ ተወላጆችን ማደን ጀመሩ፣ ንብረት ዘረፉ፣ ኣቃጠሉ፣ ከኣምስት መቶ በላይ የሚሆኑ ለብዙ ኣመታት በቦታው ነዋሪ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች በወረዳው ኣስተዳዳሪዎች እና የጸጥታ ሃይሎች ኣዝማችነት ኣሰቃቂ ጥቃት ደረሰባቸው።

በወቅቱ የኣማራ እና የቅማንት ብሄር ግጭት ተፈጥሮ የነበረ በመሆኑ የፌደራል መንግስት ኣንድ በሚኒስትሮች የተመራ ቡድን ከክልሉ ኣስተዳዳሪዎች ጋር በመሆን ወደ ቦታው በመምጣት ለማረጋጋት የተሞከረ ሲሆን የትግራይ ተወላጆችን ለቅሶ እና መከራ ለመፍታት የሞከረ ኣካል ኣልተገኘም ብቻ ሳይሆን ችግሩ ለመፈጠሩም በፌደራልም በክልልም እውቅና መስጠት ኣልተፈለገም። ይሄንን ኣቤቱታ የቀረበላቸው የክልሉ ኣስተዳዳሪዎችም (ገዱ ኣንዳርጋቸውን ጨምሮ) እና የብኣዴን ሊመንበር እና የኣገሪቱ ምክትል ጠ/ሚ የሆነውን ደመቀ መኮነን ሰምተው እንዳልሰሙ መሆን መረጡ። በክልሉ የተነሳው የቅማንት እና የኣማራ ብሄር ግጭትን ኣስመልክቶ የሰላም ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን በትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ኣሰቃቂ ግፍ ኣንድም ባለስልጣን (የክልሉም የፌደራል መንግስትም) እንደ ጉዳይ ሊያነሱት ኣልተፈለገም። ይባስ ብሎ ለሁሉም ዜጎች ቆሚያለሁ የሚለውን የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ተብየውም የኣማራና የቅማንት ግጭት ሰፊ ሪፖርት ለፓርላማው ያቀረበ ሲሆን በትግራይ ተወላጆች የደረሰውን ግፍ በስሙ ለመጥራት ባለመፈለጉ “በኣካባቢው የሚኖሩ ኣንዳንድ ውሁዳን ብሄሮችም የግጭቱ ሰለባ ሆኗል” ሲል ሸፋፍኖ ማለፉን ይታወሳል።

እርግጥ ነው በክልሉ ነዋሪ በሆኑት የትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰው ግፍ ይህ የመጀመሪያው ኣልነበረም። የትግራይ ተወልጆች የሚበዙበት እያለ (በ1994 እና በ2007 ዓ/ም የስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣውን መረጃ ይመልከቱ) የህገ መንግስቱን ኣንቀጽ 39 ቁ፣3 በመጣስ ወደ ኣማራ ክልል ኣስተዳደር የተከለለው ኣብርሃ ጅራ እና በትግራይ የወልቃይት እና ጸገዴ ኣዋሳኞችም በጠራራ ጸሃይ ተመሳሳይ ግድያዎች እና ግፍ እንደተፈጸሙ ህዝቡ ራሱ መግለጹን ይታወሳል ይህ ልዩ የሚያደርገው ግን በመላው ጎንደር፣ ባህርዳር እና ኣካባቢው የነበሩ የትግራይ ተወላጆች የዘር ማጽዳት ዘመቻ በእወጃ የተጀመረበት ኣጋጣሚ በመሆኑ ብቻ ነው።

ይህ በእነ ኣቶ ገዱ እና ብኣዴን ውስጥ በተፈጠረው የትምክህተኞች ኣረም የተመራው የዘር ማጽዳት ዘመቻ በወሳኝ መልኩ ከ20 ሺህ በላይ የትግራይ ተወላጆችን በማፈናቀል፣ በማጥቃት፣ ንብረታቸውን በማውደም እና በምዝረፍ የተጠናቀቀ ሲሆን በብኣዴን የሚመራው የክልል መንግስትም ይህ ጥቃት ለመደረሱ እስከ ቅርብ ሳምንታት ድረስ እውቅና ኣልሰጥም ብሎ ከሶስት ወራት በላይ ቆይቷል። የፌደራል መንግስቱም በተመሳሳይ እውቅና ለምስጠት ቀርቶ ቀኑን ሙሉ የኣውሮፓ ኳስ ሲዘግቡልን የሚውሉትን የመንግስት የመገናኛ ብዙሃንም ኣንድ መስመር ዜና ሊዘግቡለት ፍቃደኛ ሆነው ኣልተገኙም።

በታሪክ ኣጋጣሚ የትግራይን ብሄር ብቸኛ የፖለቲካ ወኪል ሆኖ የክልሉን መንግስታዊ ስልጣን የተቆጣጠረው ህወሓትም የትምክህተኛውን ጥቃት የደረሰበትን ህዝቡን መከታ ሆኖ ድምጹን እንደማሰማት ነገሮችን በመሸፋፈን በተገኘው ኣጋጣሚ የትግራይ ህዝብን እና ህወሓትን ለመናድ ሌት ተቀን እየሰራ ካለው ከብኣዴን ጋር መሞዳሞድ መምረጡንም ስናይ ብእጅጉ ኣዝነን ቆሽታችን ኣርረዋል። እንደሚታወቀው ብኣዴን ኣማራ በሌላ ክልል ተፈናቀለ ተጠቃ በማለቱ የፓርላማ መወያያ ኣርስት ኣድርጎ ከብሄሩ ተወላጆች ጎን በመቆም ፍትህ ሲያስገኝ ያየን ጊዜ ብኣዴኖችን ኣድንቀናል። ያለመታደል ሆኖ ይህ መልካም ህዝባዊ ተግባር በትግራይ ተወላጆች ላይ ሲሆን ኣልሰራም። የብሄሩ ወካይ የሆነውን ህወሓትም ይህ የህገ መንግስት ጥሰት ወደ ፓርላማ ኣቅርቦ ማወያየት ኣልፈልገም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለወደመው እና ለጠፋው የሰው ሂወት እና ንብረት ኣንድም ባለስልጣን ተጠያቂ ሳይደረግ በዘር የማጽዳት ዘመቻ ላይ የዋልቱን ቱባ ባለስልጣናትም ጭምር ኣሁንም በስልጣን ላይ መቀጠላቸው ስናይ ኣጅግ ኣስፈሪ ሁኔታ ውስጥ እንደገባን እና ኣገሪቱ ተጠያቂነት እና የህግ የበላይነት የሚባል ፈጽሞ እንደሌላት ኣረጋግጠናል። ይህ እጅግ ኣሳዛኝ እና ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው። ከ20 ሺህ ህዝብ በላይ ተፈናቅሎ፣ ንብረት ተዘርፎ፣ ተቃጥሎ ተጠያቂ ሊኖር ሲገባ “የትግራይ ብሄር ብቻ ኣይደለም የተቃጠለው፣ የተገደለው፣ የተዘረፈው፣ የኣማራም ጭምር ነው” በማለት የኣማራ ተጎጂ ህዝብም ፍትህ የማያስፈልገው እስኪመስል የፍትህን በር ጥርቅም ኣድርገው ዘግተውበታል። እንግዲያውስ ተጠያቂነት እና የህግ የበላይነት ያልተከበረበት ኣገር እንደ ኣገር ለማስቀጠል እጅግ በጣም ኣስቸጋሪ በመሆኑ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ቀጣይ ትግል እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ያስፈልጋል።

በትህትናቸው የምናውቃቸው የኣገሪቱ ጠ/ሚ የሆኑት ሃ/ማሪያም ደሳለኝም ትንሽ እንኳን ሳይሰቀጥጣቸው ስድስት የትግራይ ተወላጅ ብቻ ነው የሞቱት ብለው የደረሰውን ጉዳት ለማቃለል ሲሞክሩ ስናይ በቃ እውነትም ህዝባችን ከባድ እና ኣሳሳቢ ችግር ውስጥ ገብቷል ብለን እንድንደመድም ተገደናል። ጠ/ሚኒስትሩ ምን ነካቸው …!? በእሬቻ በዓል ለደረሰው ጉዳት የሃዘን ቀን ታውጆ የኣገሪቱን ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንዲሰነብት የተደርገው እኮ የወደመውን እና የሞተውን ለማስመለስ ሳይሆን ለችግሩ ከልብ የመነጨው ሃዘኔታ እና ኣገራዊ እውቅና ልምስጠት ያክል ነበር። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብዚህ ደረጃ ዘግናኝ እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኣንድ ብሄር መፈናቀል፣ ስደት፣ ዝርፊያ፣ ግድያ፣ ጥቃት ሲያጋጥም ግን የሃዘን ቀን ቀርቶ ተራ እውቅና እና ኣንድ መስመር ዜና ሳይሰጠው ሲቀር ህዝቡን እጅግ ያሳዘነ ሁኔታ ሆኖ ማለፉን ማን ይንገራቸው!

የሆነ ህኖ ህዳር 29 የህልውናቸው ዋስትና ይሆን ዘንድ የኢፌዴሪ ሕገመንግስት የፀደቀበትንና የኢተዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ሆኖ እነዲከበር መወሰኑን የሚታወቅ ነው። እዚህ ለመድረስ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አስከፊ የነበረውን ስርዓት ለመገርሰስ በከፈሉት እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ የትግራይ ህዝብ የኣንበሳውን ድርሻ ይይዛል። ከማንም በፊት ወደ ትጥቅ ትግል በመሰለፍ ከ60 ሺህ በላይ ሂወት፣ ከመቶ ሺህ በላይ ኣካል የመጉደል፣ በገንዘብ የማይገመት የንብረት ውድመት፣ ኣስከፊ ስደት፣ መንግስት ሰራሽ ረሃብ እና የተፈጥሮ ሃብትን ውድመት ደርሶበታል። ኣሁንም ሰላም እና ጦርነት ባሌለበት ሁኔታ ከኤርትራ ጋር ተፋጥጦ ሌላ የመልማት ኣማራጭ ያልቀረበለት እና የመላው ኢትዮጵያ ኣስከፊ የጸጥታ ችግር ተሸክሞ እየኖረ ያለ ህዝብ ነው።

ለዚህ ኣገር ይሄን የመሰለ ከባድ መስዋእት ከፍሎ ትርፍ ያልጠየቀው ህዝብ የልጆቹን ሂወት በከፈለበት የኣማራ ክልል ውስጥ እንዲህ ኣይነት ዘግናኝ በደል ደርሶበት ማየት ኣሳዛኝ እና ለታሪክ የሚተርፍ ጠባሳ የፈጠረ ሆኖ እናገኘዋለን። በተጠቀሰው ቦታም ህዳር 29 የብሄር ብሄረሰቦች በዓል “ለናንተ ኣይመለከትም” ተብለው በግፍ የተባረሩበት ቀን ሆኖ ኣልፈዋል። “የወጋ ቢረሳ የተወጋ ኣይረሳም” ቢባልም የትግራይ ህዝብ በደልን የመርሳት ባህሉ ጥልቅ መሆኑን ያስመሰከረ ህዝብ ነው። ሊያርዱት የመጡት ሳይቀር ማርኮ ምህረት በመስጠት ሰንጋ ኣርዶ የሸኘ ህዝብ መሆኑን ይታወቃል። ሆኖም መጪው ትውልድ ይማርበት ዘንድ ይህ በደል ታሪክ ሰንዶታል።

ነገር ግን ኣሁንም የሆነውን ሆነ‘ና *ተጠያቂነት ይኑር እንላለን። *ፍትህ ለተበደለው ህዝብ፣ ፍርድ ለወንጀለኛ ባለስልጣኖች ይሰጥ ዘንድ እንጠይቃለን።
ሰናይ ሳምንት!
ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ