Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

አዋጁ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና ዋስትና የሰጠ መሆኑን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት አስታወቀ

command-post
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 21 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ህዝብን ለመምራት የሚያስችል ሰላምና መረጋጋት ያሰፈነ በመሆኑ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና ዋስትና የሰጠ መሆኑን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት አስታወቀ።

ሰላማዊ ትግልን ግብ አድርገው በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፥ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያ ከኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

ፓርቲዎቹ በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሳውን ሁከት እና ብጥብጥ ተከትሎ ተግባራዊ በሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ያላቸውን ጥያቄ እና ስጋታቸውን ማዕከል አድርገው ነው የመከሩት።

በመድረኩ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ህልውና ላይ ስጋትን የደቀነ ነው የሚሉ እና ሌሎችም ጥያቄዎች ቀርበዋል።

የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳም፥ የአዋጁ ግብ የሃገሪቱን የቀደመ ሰላም መመለስ እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ስጋትን መደቀን አይደለም ብለዋል።

በፈረሰ ሀገር ህዝብ መምራት አይቻልም ያሉት ሚኒስትሩ አዋጁ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ህልውና ዋስትና የሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

ምንም የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳናደርግ ታግደናል የሚሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹም፥ አዋጁ የተለመደ የፓርቲ ስራዎችን እንዳናከናውን እንኳን ቦታ የነፈገ ነው የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

የመድረክ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር እና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ገብሩ ገብረማርያም እንዳሉትም፥ ይህንን ሁኔታ ተከትሎ አንዳንድ ፓርቲዎች የፈቃድ ሰነዳችንን እንመለስ እስከማለት መድረሳቸውን ይናገራሉ።

ይሁንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተለመደው የፓርቲ ስራ አንስቶ በኮማንድ ፖስቱ ፈቃድ አግኝተው ሊከናወኑ እስከሚችሉ ተግባራት ድረስ ያልተደረጉ ክልከላዎች ይዘት ተብራርቶልናል ነው ያሉት።

የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በበኩላቸው፥ በተቃዋሚ ፓርቲዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሙሉ ይዘት በአግባብ ያለመረዳት ችግር መኖሩን ጠቅሰው ይህ ሁኔታም ፓርቲዎቹ ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይ ተንጸባርቋል ይላሉ።

የመናገር መብታችን ታፍኗል፣ መግለጫ እንዳትሰጡ፣ አትሰብሳቡ ተብለናል የሚሉ ቅሬታዎች መቅረባቸውም የዚህ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተከለከለ የህትመት ውጤት አለመኖሩን የጠቀሱት አቶ ሲራጅ፥ ሁከት ቀስቃሽ ቅስቀሳ እንጂ መቀስቀስ እንዳልተከለከለና ከአሸባሪ ድርጅት ሚዲያዎች ውጭም የታገደ ልሳንም ሆነ የታፈነ ሀሳብ እንደሌለም ገልጸዋል።

በቀጣይ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ፓርቲዎች በሚያካሂዷቸው እንቅስቃሴዎች መንግስት ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች እምነታቸው መሆኑን የገለጹት የአሮሞ ነጻነት ብሄራዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ክፍለማርያም ሙሉጌታ ደግሞ፥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሀገሪቱን ከብጥብጥ ወደ ስክነት የመለሰ ነው ብለዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አዋጁ ዙሪያ የተደረገው ውይይት ግልጽነትና መግባባት የፈጠረ መሆኑን የተናገሩት የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ፥ መሰል መድረኮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አንስተዋል።

አዋጁ የታለመለትን ግብ እየመታ ነው ያሉት አቶ ሲራጅም፥ በሃገሪቱ የታየውን ለውጥ ተከትሎ ገደቦች መነሳታቸውን ይጠቅሳሉ።

ከዚህ ባለፈ ግን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እንደዚህ አይነት ውይይት ማካሄድ፥ በፓርቲዎቹ እና በደጋፊዎቻቸው ላይ የተሻለ ግልጽነትን በመፍጠር የሃገሪቱን ሰላም እንደቀደመው ጊዜ አስተማማኝ ለማድረግ ፋይዳው ትልቅ መሆኑን ያስረዳሉ።