Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በጋምቤላ ክልል ለኢንቨስትመንት ከሚሰጥ መሬት ጋር ተያይዞ ችግሮችን የመፍታት ስራ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 17 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ለግብርና ኢንቨስትመንት ከሚሰጥ መሬት ጋር ተያይዞ በጥናት የተለዩ ችግሮችን የመፍታት ስራ ተጀመረ።

በክልሉ ከሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ በተደረገ ጥናት በርካታ ችግሮች እንዳሉ ተለይተዋል።

ይህም ዘርፉ በሚጠበቀው ልክ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሚናውን እንዳይጫወት ከማድረግ ባለፈ ብልሹ አሰራሮች እንዲስፋፉና የሃብት ብክነት እንዲስተዋል አድርጓል።

ችግሩን ለመለየት በተደረገ ጥናትም፥ አንድ ይዞታን ለበርካታ ባለሃብቶች መስጠት፣ የመሬት አቅርቦት ዝግጅት ያለመኖርና በደላሎች እጅ መውደቁ በጥናቱ ከተለዩት ውስብስብ ችግሮች መካከል ተጠቅሰዋል።

ጥናቱ ችግሮችን በማመላከት ገቢራዊ ቢደረጉ ለውጥ የሚያመጡ ምክረ ሃሳቦችንም አስቀምጧል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሎዋክ ቱት ኮት፥ ክልሉ የመሬት አቅርቦትና አሰጣጥ ስራው ስርዓት እንዲበጅለት ማድረግና የህግ ክፍተት ያለባቸውን የማስተካከል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ በመሆኑ ብቃት ባላቸው አመራሮችና ባለሙያዎች መልሶ እንዲደራጅ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ባለሃብቶች የወሰዱትን መሬት በሙሉ አቅማቸው እንዲያለሙ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ የሚደረግበት ስርዓት እየተዘረጋ ሲሆን፥ መሬት ወስደው ወደ ልማት የማይገቡና የዘርፉ ዕድገት ላይ ችግር እንዲፈጠር የሚያደርጉ ግለሰቦች ከዘርፉ እንዲወጡ የሚደረግ ይሆናልም ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም ችግር እንዲፈጠር ያደረጉ አምስት አመራሮችና ስምንት ባለሙያዎች ላይ የእርምት እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በህገ ወጥ ተግባሩ ተሰማርተው የነበሩና ለጊዜው አካባቢውን ለቀው የተሰወሩ ግለሰቦችም በህግ ክትትል እየተደረገባቸው እንደሚገኝ በመጥቀስ።

በዘርፉ ችግር እንዲፈጠር ያደረጉ ደላሎችም በአሁኑ ወቅት ማንነታቸው ተለይቶ በቅርቡ በህግ እንዲጠየቁ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

በቀጣይም እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ በአሰራርና አደረጃጀት ያሉ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ እያደረገ እንደሚሄድም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታሁን ናና በበኩላቸው፥ ተደራርበው ለተወሰዱ የኢንቨስትመንት መሬቶች ብድር መስጠት በትግበራ ሂደት የተፈጠሩ መሆናቸውን ያነሳሉ።

በልማት ባንኩ አሰራር መሰረት አንድ ብድር የተፈቀደለት ባለሃብት ብድሩን የሚያገኘው በተለያዩ ዙሮች ነው።

ባለሃብቱ በመጀመሪያው ዙር ከባንኩ የተለቀቀለት ገንዘብ ስራ ላይ ማዋሉን የሚያረጋግጥ ሪፖርት ለልማት ባንኩ ሲያቀርብና ሲረጋገጥ ከብድሩ በሁለተኛ ዙር የሚለቀቅለትን ገንዘብ ያገኛል።

በባንኩ ጋምቤላና ጅማ ቅርንጫፎች የተደረገው ከዚህ በተቃራኒው ሲሆን፥ ከልማት ባንኩ ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር በመጀመሪያው ዙር የተለቀቀው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ሳይውል በሃሰት የስራ ሪፖርት ሁለተኛው ዙር ገንዘብ ለባለሃብቶች ይለቀቅ ነበር።

ይህን ባንኩ ላበደረው ገንዘብ በቂ መሬት ላይ ያረፈ ነገር ማስተማመኛ እንዳይኖረው ማድረጉን ነው አቶ ጌታሁን የሚናገሩት።

በድርጊቱ እንደተሳተፉ የተደረሰባቸው የልማት ባንኩ ባለሙያዎች እንዲባረሩ መደረጉን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፥ በቀጣይ በህግ እንዲጠየቁ መረጃቸው ለህግ እንደሚተላለፍ አንስተዋል።

ለብልሹ አሰራር በር በመክፈት ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ክፍተቶችን በመለየት የማስተካከልና ጠንካራ ክትትል እንዲኖር የሚያደርግ የአሰራር ስርዓት ልማት ባንኩ በቀጣይ ይከተላልም ብለዋል።

የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ደግሞ፥ ከባለሃብቶች ምልመላ ጀምሮ ያሉ ክፍተቶች ከእነመፍትሄያቸው የቀረቡ በመሆኑ እንዲተገበሩ እንደሚደረግ ይገልጻል።