Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ 9 ሺህ 800 ተጠርጣሪዎች የፊታችን ረቡዕ ይለቀቃሉ


አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ስር ውለው ስልጠና የተሰጣቸው 9 ሺህ 800 ተጠርጣሪዎች የፊታችን ረቡዕ እንደሚለቀቁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።

የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ስልጠና ወስደው ከሚለቀቁት በተጨማሪ ሌሎች 2 ሺህ 449 ተጠርጣሪዎች ደግሞ በህግ የሚጠየቁ ይሆናል ብለዋል።

ከአዋጁ ወዲህ የሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል የታየበት መሆኑንም የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ገልፀዋል።

በመግለጫው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወደ ተግባር ከገባ ጀምሮ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በርካታ ሰራዎች መሰራታቸው ተነስቷል።

ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ከማዋል ጀምሮ በሁከቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማትና አገልግሎት መስጪያዎችን መልሶ የማቋቋም ሰራዎች መከናወናቸውንም ነው አቶ ሲራጅ የገለጹት።

በዚህም በአንደኛው ዙር በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች ውሰጥ በአምስት ማሰልጠኛ ማእከል የሰለጠኑት 9 ሺህ 800 ያህሉ ናቸው።

እነዚህ ሰልጣኞችም በሚፈለገው ደረጃ መሰልጠን መቻላቸውን ተከትሎ ነው የፊታችን ረቡዕ ይለቀቃሉ የተባለው።

እነዚህ ተጠርጣሪዎች በሚፈለገው ደረጃ የሰለጠኑና በስራቸው የተጸጸቱ በመሆናቸውም እንዲለቀቁ መወሰኑንም የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ተናግረዋል።

በማወቅና ባለማወቅ በሁከቱ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎች በስልጠና እንዲለቀቁ እንደ መደረጉ ሁሉ 2 ሺህ 449 የሚሆኑት ደግሞ በሁከቱ የነበራቸው ተሳትፎ በህግ ተጠያቂ የሚያደርጋቸው በመሆኑ በህግ የሚጠየቁ ይሆናል ብለዋል።

ከዚህ ውጪ የተለያዩ የሽብር ቡድኖችም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረገ ሲሆን እስካሁን 19 ሽብር ለመፍጠር የተንቀሳቀሱ ቡድኖችን መያዝ ተችሏል።

አቶ ሲራጅ በመጀመሪያው ዙር የተሰወሩ ተጠርጣሪዎችና አዋጁም ከወጣ በኋላ አዋጁን የተላለፉና በሁከት ውስጥ ያሉ አካላትን የመያዙ ተግባር ቀጠሏል ነው ያሉት።

በዚህም በሁለተኛ ዙር 12 ሺህ 500 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህም በቁጥጥር ስር ባሉበት ዞን በስልጠና የሚለቀቁ ወይም በህግ የሚጠየቁ ናቸው የሚለውን የመለየት ስራ እየተሰራ ሲሆን፥ እስካሁን የተለዩ 4 ሺህ 000 ተጠርጣሪዎች በምዕራብ ሸዋ አዲስ በተቋቋመው የሰንቀሌ ማሰልጠኛ እንዲገቡ ይደረጋል ነው ያሉት አቶ ሲራጅ።

የተቀሩትንም በመለየት በአንደኛው ዙር ሰልጥነው በሚወጡት ማሰልጠኛ እንዲገቡ ተደርጎ ነው ሰልጥነው የሚለቀቁት ተብሏል።

በዚህ ውስጥ በህግ ሊጠየቁ የሚገባቸውም በህግ እንዲጠየቁ የማድረጉ ተግባር መቀጠሉም ተጠቁሟል።

ኮማንድ ፖስቱ 18 የፀጥታ ሀይሎች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደረገ ሲሆን፥ የስነ ምግባር ችግር ያለባቸው 12 የፀጥታ ሀይሎች ላይም የዲሲፕሊን እርምጃ መውሰዱንም ገልፀዋል።

አዋጁን ተላልፈው የፀጥታ ሀይሎችን ልብስ ለብሰው ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 10 የፀጥታ ሀይሉ አባል ያልሆኑ ሰዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።

በመግለጫው የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ላይ ምን ተጨባጭ ለውጥ አመጣ?

ከሞባይል ኢንተርኔት ጋር ተያየዞ የነበረው ስጋት ምን ያህል ተቃሏል? የሚሉት ይገኝበታል።

አቶ ሲራጅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጨባጭ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ማስቻሉን ያነሱ ሲሆን፥ ከሞባይል ኢንተርኔት ጋር ተያይዞ የሁከት ተግባር የሚፈጽሙትን የሚቆጣጠርበት ስርዓት መዘርጋቱን አንሰተዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተተገበረ ጀምሮ የመጡት እያንዳንዱ ውጤቶች ህዝብን መሰረት ያደረገ ነው ያሉት አቶ ሲራጅ፥ ይህን የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለማድረስ አሁን ላይ የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የአዋጁ መነሳት አለመነሳት የሚወሰነውም በመጣው ለውጥ ብቻ ሳይሆን በሚያመጣው አስተማማኝ የሰላምና መረጋጋት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።