Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በአዲስ አበባ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 125 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 17 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 125 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ በመዲናዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት እንቅስቃሴዎች በሚፈለገው ፍጥነትና የህዝብ እርካታን ሊያመጣ በሚችል አቅጣጫ እንዳይጓዝ እቅንቀፋት ከሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ውስጥ በተለያዩ የመንግስትና የአስተዳደር አካለት ውስጥ በአንዳንድ የመንግስት ሰራተኞች በተለያየ ደረጃ የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች ዋነኛዎቹ እንደሆኑ ጠቁሟል።

ችግሮቹን በመሰረታዊነት ለመቅረፍ መንግስት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀመራቸው የመልካም አስተዳደር እና የጥልቅ ተህድሶ ንቅናቄ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ነው መግለጫው ያስታወቀው፡፡

ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው ባለድረሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጀመረውን ሰፊ ንቅናቄ መነሻ በማድረግ ዓርብ ታህሳስ 7 ቀን 2009 ዓ/ም ባደረገው ዘመቻ በተለያዩ የከተማው አስተዳደር መስሪያ ቤቶች ውስጥ በተፈፀመ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 125 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በፖሊስ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከልም 22 አመራሮች፣ 99 ሰራተኞች እና አራት ግለሰቦች መሆናቸውን የኮሚሽኑ መግለጫ ያስረዳል፡፡

የመንግስት ቤት ወደ ግለሰቦች እንዲዞር ማድረግ ፣ በህ-ገወጥ መንገድ የተሽከርካሪ ሰሌዳ መስጠት ፣ በሌሉ ሰዎች ስም መንጃ ፍቃድ መስጠት ፣ የመንግስት ገንዘብ ማጉደል ፣ ከህግና አሰራር ስርዓት ውጪ ለግለሰቦች ያለጨረታ ስራዎችን መስጠት ግለሰቦቹ ከተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች ውስጥ እንደሚገኙ ተመልክቷል።

የከተማው ነዋሪ በተለያዩ መድረኮች የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲባባሱ ያቀጣጣይነት ሚና ያላቸው እንዚህ የወንጀል ድርጊቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የህብረተሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚናት የሚያሳጡ መሆናቸውን ያነሳው ኮሚሽኑ ህዝቡ ይህን ተገንዝቦ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል ኮሚሽኑ የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ በከተማ ውስጥ የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎችን በማጋለጥና መረጃ በመስጠት ህዝቡ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።

የሙስና ወንጀል ድርጊቶችን በኮሚሽኑ ስልክ ቁጥር 01-11-56-83-11 ወይንም በአካል ቀርቦ መጠቆም እንደሚችልም ነው ያስታወቀው።የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስም በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩትን ግሰለቦች፥ በቁጥጥር ስር በማዋል በዛሬው እለት ለጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት አቅርቧቸዋል።