Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ስልጣንን አለአግባብ በተጠቀሙና በብልሹ አሰራር በተዘፈቁ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ገለፁ

hd-new-pic
አዲስ አበባ፣ ህዳር 29፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ስልጣንን አለአግባብ በተጠቀሙና በብልሹ አሰራር በተዘፈቁ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።

በሃገሪቱ የተከሰተውን ሁከት ለማስቆም ተግባራዊ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ላይ ምንም አይነት ተፅእኖ እንዳላሳደረም ተናግረዋል።

በኢህአዴግ ምክር ቤትና ስራ አስፈፃሚው በህዝቡ ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታትና ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌን ለማስወገድ የተቀመጠው በጥልቀት የመታደስ አቅጣጫ በመግባባትና በጥሩ መንፈስ እየተካሄደ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

እስካሁን የተወሰዱት እርምጃዎች ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መሆናቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ስልጣናቸውን አላግባብ በተጠቀሙና በብልሹ አሰራር በተዘፈቁ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ተግባር እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የተከሰተውን ሁከት ለማስቆም ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሃገሪቱን ወደ ቀድሞ ሰላሟ መመለሱንና ለውጤቱ መገኘትም የህዝቡ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት።

በክልሎች እና ወደ ታች ባሉ የመንግስት መዋቅሮች በአዲስ መልክ የማደራጀት ስራው በተገቢው መንገድ እየተከናወነ እንደሆነም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ11ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን አደረሳችሁ የሚል መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ የተዛቡ አመለካከቶችን ወደ ጎን በመተው አገራዊ አንድነትን የበለጠ ማጎልበት እንደሚገባ ገልፀዋል።

ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ በአንድነት በማስቀጠል አገሪቱን ወደ ተሻለ ምእራፍ ማሸጋገር ይገባል ብለዋል።

የብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት የተፈጠረበት፣ በአገሪቱ የነበሩ የተዛቡ አመለካከቶች የተወገዱበትና አንድ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማሕበረሰብ ለመፍጠር መሰረት የተጣለበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በዓሉ አገራዊ አንድነትን የበለጠ የሚጎለብትበት እንዲሁም ሕብረ ብሔራዊነት የሚጠናከርበት ነውም ብለዋል።