አዲስ አበባ፣ ህዳር 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በመሪዎች ደረጃ ንግግር ሊያደርጉ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ ግንኙነት ዙሪያ ለመምከርም ዛሬ ወደ ሪያድ አቅንተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በቆይታቸው ከሀገሪቱ ንጉስ ሳልማን ቢን አብዱላዚዝ አል ሳውድ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
ንግድና ኢንቨስትመንት፣ የፀረ ሽብር ትግል እንዲሁም ቀጠናዊ የፀጥታ ጉዳዮች ደግሞ ዋናው የመነጋገሪያ አጀንዳቸው እንደሚሆን ነው የተነገረው።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ሳዑዲ አረቢያ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክሩ ይሆናል።