አዲስ አበባ፣ ህዳር 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቻይናው ምክትል ፕሬዚዳንት ሊ ዩዋን ቻኦ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ገቡ።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ በቆይታቸው ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ እና ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር በሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ተሳታፊ በሚሆኑባቸው መንገዶች ዙሪያ እንደሚመክሩም ነው የሚጠበቀው።
ከዚህ ባለፈም የአዲስ አበባን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማስፋት የሚያስችል የብድር ስምምነት ከቻይና መንግስት ጋር ይፈረማል ተብሏል።
በተጨማሪም የባቡር አካዳሚ ለመገንባት የሚያስችል ድጋፍ ከቻይና መንግስት ለማግኘት ስምምነት እንደሚደረግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
የምክትል ፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በሃገራቱ መካከል ያለውን ስትራቴጂያዌ አጋርነት የሚያንጸባርቅ እና በሃገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር እንደሆነም ታምኖበታል።