አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በዘንድሮው ዓመት የ24 ሰዓት የሳተላይት ቴሌቪዥን ፕሮግራም ስርጭት ለመጀመር መዘጋጀቱን አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም እንደገለጹት ሳይንስን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሳተላይት ቴሌቪዥን ፕሮግራም ስርጭት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ባለፈው አንድ ዓመት በተቋሙ ሕንጻ ለሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት የሚረዱ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት አውታሮች ተዘርግተዋል ነው ያሉት።
ከዚህ ውስጥ አንዱ የሚዲያ ማዕከል መሆኑን ጠቁመው ማዕከሉ ለሕትመትና ለብሮድካስት ሚዲያ በሚያገለግሉ ዘመናዊ መሳሪያዎች ተደራጅቷል ብለዋል።
ለሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት የሚረዳ ዘመናዊ ስቱዲዮ በሚዲያ ማዕከሉ ግንባታው መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በተገነባው ሕንጻ ላይ የተተከለው ባለ 84 ራክ የመረጃ ቋት (ዳታቤዝ) ለሚዲያ የሳተላይት ስርጭትም ሆነ ለተጠሪ መስሪያ ቤቶች ያገለግላል፤ ይህ መሆኑ ሚኒስቴሩን ”ከዕርምጃ ወደ ሩጫ” መሸጋገሩን የሚያመለክት አይነተኛ መገለጫ ነው ብለዋል።
የሚዲያ ማዕከሉ የሳተላይት ስርጭቱን በአማርኛ፣ ኦሮምኛና ትግሪኛ ቋንቋዎች እንደሚጀምርም ነው አቶ ወንድወሰን የጠቆሙት።
በቀጣይም በሌሎች የሀገሪቱ ቋንቋዎች ስርጭቱን የማስፋፋት እቅድ እንዳለ ገልፀው የፕሮግራሙ ይዘትም ሕዝብ በቀላሉ እንዲገባውና እንዲያውቀው በሚችለው ቀላል ቋንቋና አዝናኝ አቀራረብ እንደሚሆን አብራርተዋል።
ከስርጭት መርሃግብሮች ውስጥ የልጆች ፕሮግራም የሚያካትትና የሕጻናትን የፈጠራ ተነሳሽነት የሚያሳድግ ይዘት እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
የመረጃ ምንጮችን በተመለከተም በሚኒስቴሩ ስር ያሉ 10 ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም በአዲስ አበባና በአዳማ የልህቀት ማዕከላት ሁለቱ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
በአገር ቤትና በውጭ የሚገኙ የምርምር ተቋማትና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን እንደ መረጃ ምንጭነት የመጠቀም ዝግጅት መኖሩንም ተናግረዋል።
የሚዲያ ማዕከሉ አራት ራሳቸውን የቻሉ ክፍሎች ያሉት ሲሆን በአሁኑ ወቅት የዘገባ ውጤቶቹን ቴክሳይንስ በሚል ርዕስ በኢቢሲ፣ በመጽሔት እንዲሁም በፌስቡክ፣ በዩቲዩብና በትዊተር ለሕዝብ እያስራጨ ይገኛል።
በቅርቡም የሬዲዮ ስርጭት ዳግም ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ታውቋል።
የሚዲያ ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ የሳተላይት ስርጭት ስራ ለመጀመር የሚያስችሉ ቁሳቁሶች ከውጭ እያስገባ እንደሚገኝም ተገልጿል።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ላለፉት 40 ዓመታት ይከተል የነበረውን “ሳይንስና እርምጃው” መርህ በቅርቡ “ከዕርምጃ ወደ ሩጫ” በሚል መተካቱ ይታወሳል።