አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የመንግስት ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም ከማዋል ይልቅ ለግል ጥምቅና ክብር መጠቀም የሁሉም ችግሮች ምንጭ በመሆኑ ይህንን ለማሰወገድ እንደሚሰሩ አረጋገጡ።
ከፍተኛ አመራሮቹ ለስምንተ ቀናት ሲያካሂዱት የነበረውን በጥልቅ የመታደስ ንቅናቄ ስብሰባቸውን ትናንት ማምሻውን አጠናቀዋል።
በማጠናቀቂያው ላይ ባወጡት መግለጫም ስብሰባው የህዳሴ ጉዞ፣ በድርጅቱ ላይ የተጋረጡ አደጋዎችና ፈተናዎች፣ የህወሓት የስራ አስፈፃሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ ግምገማ እና ቀጣይ የትግል አቅጣጫ የሚሉ አጀንዳዎችን በስፋ ተመልክቷል።
በግምገማቸው ባለፉት 15 ዓመታት በክልሉ የተከናወኑ የልማት ስራዎች እና የተዘመዘገቡት ድሎች ድህነት እንዲቀንስ ማስቻላቸውን አንስተዋል።
በ1991 ዓመተ ምህረት ላይ በክልሉ 56 በመቶ ነበረው ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ህዝብ 2007 ላይ ወደ 23 በመቶ መውረዱ ነው የተገለፀው።
እነዚህ ታላላቅ ስኬቶች እንዳሉ ሆኖ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንደነበሩም ተመልክቷል።
በተለይም የዴሞክራሲ ተቋማት ሊደርሱ በሚገባቸው ደረጃ ላይ አለመድረሳቸው እና በመልካም አስተዳደር እጦት ህዝብ ለምሬት መዳረጉ ተጠቅሷል።
እነዚህ ሁኔታዎች በድርጅትና በህዝብ እንዲሁም በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለው መተማመን እንዲሸረሸር አድርጓል ብለዋል።
ኪራይ ሰብሳነትን ለማጥፋት ተከታታይ ትግል አለማድረግ፣ የፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት እና ተግባር፣ የውስጠ ድርጅት ትግል መቀነስ፣ አድርባይነት እና ብልሹ አሰራር እንዳሉ ተገምግሟል።
ስልጣን ለህዝብ ጥቅምና አገልግሎት ከመዋል ይልቅ ለግል ጥቅምና መገልገያነት መጠቀም ለሁሉም ችግሮች መነሻ በመሆኑም አመራሮቹ እንደሚታገሉ ነው ያረጋገጡት።
በቀጣይ የወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥም የድህት ቅነሳ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል።
የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማጎልበት እና በመንግስት የስራ ሀላፊዎች ላይ የሚካሄደውን ክትትልና ቁጥጥር ለማጠናከር ምክር ቤቶች ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ የደረጋልም ነው የተባለው።
በተጨማሪም የሲቪክ ማሀበራት፣ የመገናኛ ብዙሃን እና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱም እንሰራለን ብለዋል።
የተጀመረው የተሃድሶ ንቅናቄ ወደ ህዝቡ እንደሚወርድ ያመለከተው መግለጫቸው፥ ህዝቡም ያለምህረት ለመግምገምና ለማረም በንቅናቄው እንዲሳተፍ ከፍተኛ አመራሮቹ ጥሪ አቅርበዋል።