በምዕራብ ትግራይ ዞን ሰርጎ ለመግባት የሞከረው የግንቦት 7 አርበኞች የጥፋት ሀይል በዞኑ ህዝብና ሚሊሻ በቁጥጥር ስር መዋሉን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
አጠቃላይ በሁለት ዙር ከገባው 113 የታጠቀ የጥፋት የጥፋት ሀይል 15ቱ ሲገደሉ 73ቱ ሊማረኩ ችለዋል፡፡
የመጀመሪያው ዙር የተመራው ሻለቃ መሳፍንት ጥጋቡ በሚባለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ዙር ደግሞ ደስታው ተገኝ በሚባለው ግለሰብ ነበር። በወቅቱ በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ መሪዎቹን ጨምሮ ሌሎች የመሪነት ሚና የነበራቸው የጥፋት ሓይሎች ሙትና ምርኮኛ ሆነዋል።
ይዘውት የነበረው በርካታ የጦር መሳሪያ፣ተተኳሾችና ቁሳቁሶችም ሊማረኩ ችለዋል።
ከተማረከው መካከል 73 ክላሽን ኮቭ ጠመንጃ፣ 62 የእጅ ቦምብ፣ 2 ከባድ መትረየስ፣ 1 አር ፒጂ፣ 2 ስናይፐር፣ 5 ሽጉጥና 2 ቱሪያ ሳተላይት የመገናኛ መሳርያ ይጠቀሳል።
በተጨማሪ 5 የጦር ሜዳ መነፀር፣1 ዲጅታል ካሜራ፣8 መረጃ የያዙ ፍላሾች፣1 ሶላር እና 5 ተንቀሳቃሽ ስልኮች እንዲሁም በርካታ የኢትዮጵያ ብርና የአሜሪካ ዶላር ተይዟል።
የትግራይ ምዕራባዊ ዞን ህዝብና ሚሊሻ የተበታተኑትን ጥቂት የጥፋት ሃይሎች እየተከታተለ በመልቀም ላይ እንደሚገኝ የመከላከያ ሚኒስቴር በላከው መግለጫ አመልክቷል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው የሻዕቢያ፣ አርበኞች ግንቦት ሰባትም ሆነ ሌሎች የጥፋት ሓይሎች በተሳሳተ ስሌት የአገሪቷን ሰላም ማወክና ልማቱን ማደናቀፍ ፈፅሞ እንደማይችሉ ያሰተማረ መሆኑን አመልከቷል።