Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የምርጫ ህጉን ለማሻሻል ዝግጁነት መኖሩ የሁሉም ዜጎች ድምፅ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲያገኝ ይረዳል – ምሁራን

voting-reform
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 25 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚካሄዱ ምርጫዎች የሁሉም ዜጎች ድምፅ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲያገኙ ለማድረግ የምርጫ ህጉን ለማሻሻል ዝግጁነት መኖሩ በሀገሪቱ ያለውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ምሁራን ተናገሩ።
የ50 ሲደመር አንድን የአብላጫ የምርጫ ስርዓት አብላጫ ድምጽ ላመጣው እንጂ ለቀሪው 49 በመቶ ድምጽ ውክልና የማያስገኝ መሆኑን በማንሳት፥ የሁሉም ድምጽ ሊወከልበት የሚችለውን የምርጫ ስርዓት ለመከተል መንግስት ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ማክሰኞ መናገራቸው ይታወሳል። 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ደህንነት ትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት አቶ ሙሉቀን ሀብቱ፥ ሊተገበር የታሰበው የምርጫ ስርዓት ድምጻችን አልተወከለም ለሚሉ ዜጎችና ለፖለቲካ ፓርቲዎች አዲስ ተስፋ የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ስትራቴጂክ ጉዳዮች ትምህርት ክፍል ሃላፊ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ ፀሃዬ በበኩላቸው፥ መንግስት የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ስርዓትን ከአብላጫ ድምጽ ስርዓት ጋር ቀይጦ ለመጠቀም ዝግጁነት ማሳየቱ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚስማማ ነው ይላሉ።
ለዚህ ደግሞ ትልቁ የዴሞክራሲ መገለጫ መወከል በመሆኑና ይህ የምርጫ ስርዓት ውክልናን ማስገኘቱ ለተስማሚነቱ መገለጫ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ስርዓት፥ ፓርቲዎች የራሳቸውን ተወካዮች መርጠው ለድምፅ ሰጭዎች በሚያስተዋውቁበት ክፍት ስርዓት እና ዜጎች ድምፃቸውን ለፈለጉት ፓርቲ ሰጥተው ፓርቲው ራሱ ተወካዮቹን በሚመርጥበት ስርዓት እንደሚካሄድ የገለጹት ደግሞ አቶ ሙሉቀን ናቸው።
ከዚህ አንጻርም የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ስርዓትን በተገበሩ ሃገራት ያለው የስርዓቱ አንድምታ፥ ትንሽ ድምጽም ሆነ አብላጫ ድምጽ ያገኙ ፓርቲዎችን ማሳተፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
የፖለቲካል ሳይንስ እና ስትራቴጂክ ጉዳይ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ ፀሃዬ፥ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ስርዓት በየጊዜው በሚካሄዱ ምርጫዎች የዜጎችን ተሳትፎ የሚያጠናክር መሆኑን ያስረዳሉ።
በዚህ ስርዓት የመደብ፣ የጾታና ሌሎችም ውክልናዎች ሊኖሩ ስለሚችሉም፥ ድምፃችን አልተሰማም ለሚሉ ወገኖች ምላሽ የሚሰጥ መሆኑንም ነው የሚያስረዱት።
ሊተገበር የታሰበው የምርጫ ስርዓት ከተነገሩለት ጠቀሜታዎች ጎን ለጎን፥ ውክልናን የሚያመጣ በመሆኑ ከዚህ ጋር ተያይዞ የጠራ ፖሊሲ የሌላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሊያሳትፍ የሚችል መሆኑ የምርጫ ስርዓቱ ድክመት ይሉታል።
ምሁራኑ የምርጫ ህጉን ከማሻሻል ባለፈም መንግስት ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ ስራ መስራ አለበት ይላሉ።
እንደ ምሁራኑ ገለጻ ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል በትምህርት ማነፅና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያበብ እና የታሰበው የምርጫ ስርዓት ትክክለኛ ውጤት እንዲያስመዘግብ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ማስፋፋትና ማጠናከር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

One Response to የምርጫ ህጉን ለማሻሻል ዝግጁነት መኖሩ የሁሉም ዜጎች ድምፅ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲያገኝ ይረዳል – ምሁራን