Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ከኃላፊነታቸው ተሰናበቱ

devellopment-bank-get-fired
ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ኢሳያስ ባህረ፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንትነታቸው ተነሱ፡፡

ባለፈው ዓርብ ኅዳር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል ፊርማ በወጣ ደብዳቤ፣ አቶ ኢሳያስ ከፕሬዚዳንትነታቸው መነሳታቸው ተገልጾላቸዋል፡፡

‹‹የተነሳሁበት ምክንያት ግልጽ አልሆነልኝም፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን በትኩስ ኃይል እንዲመራ ለማድረግ ከሆነ ግን መነሳቴ መልካም ነው፤›› ሲሉ አቶ ኢሳያስ የተነሱበትን ምክንያት እንደማያውቁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ኢሳያስ የተነሱበት ደብዳቤ ዓርብ ከቀትር በኋላ እንዲደርሳቸው ከመደረጉ በፊት፣ ጠዋት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተመራ ስብሰባ ተካሄዶ እንደነበር ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጫኔ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ፣ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀና አቶ ኢሳያስን ጨምሮ የተለያዩ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡

የውይይቱ ዓላማ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች በሚቀርቡ የእርሻ መሬቶች፣ እንዲሁም ብድርን በተመለከተ የተፈጠሩ ችግሮች ላይ በተሰናዳ ጥናት ላይ ለመነጋገር ነበር፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተቋቋመ ኮሚቴ በተካሄደው ጥናት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሥራ አፈጻጻም በመልካም ጎኑ መነሳቱን የተናገሩት ምንጮች፣ በስብሰባው ሒደት ግን አለመግባባቶች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. የመጀመርያው ወራት በአገሪቱ እየተካሄደ የሚገኘው የግብርና ኢንቨስትመንት ሥራዎች ከማበብ ይልቅ ችግራቸው እየጎላ በመምጣቱ፣ ሙሉ ለሙሉ ለዘርፉ መሬትና ብድር እንዳይቀርብ ታግዷል፡፡

ይኼ ዕግድ ሊወጣ የቻለው በተለይ በጋምቤላ ክልል ለሚገኙ የእርሻ ኩባንያዎች የተሰጠው መሬት የተደራረበ በመሆኑ፣ በሁለት ኩባንያዎች ተደራርቦ ለተሰጠ መሬት ሁለት ጊዜ ብድር መሰጠቱ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የሙስና አመላካች ክስተቶች በመኖራቸው ነው ተብሏል፡፡

ይኼ ችግር እንዴት ሊፈጠር እንደቻለና የመፍትሔ ሐሳብ እንዲቀርብ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አማካይነት የተቋቋመው ኮሚቴ ጥናት አካሄዷል፡፡ በዚህ ጥናት መሠረት ማሻሻያዎች ተደርገው የታገደው የመሬትና የብድር አሰጣጥ በድጋሚ ይጀመራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

በዕለቱ በተካሄደው ስብሰባ ሌሎች ነጥቦች የተነሱ ቢሆንም የችግሩ ማጠንጠኛ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር፣ የመሬት አሰጣጥ ሒደትና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደግሞ በዚህ ላይ ተመሥርቶ የሚሰጣቸው ብድሮች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንደ ባንክ መርህ በመስኖ ለሚካሄዱ ሜካናይዝድ ፕሮጀክቶች ብድር መስጠት ይሻል፡፡ ነገር ግን መሬት አስተዳደር የዝናብ ጥገኛ ለሆኑ ፕሮጀክቶች ብድር እንዲቀርብ ፍላጎት አለው፡፡ መንግሥት በዝናብ ጥገኛ ለሆኑ ፕሮጀክቶችም ብድር እንዲቀርብ መመርያ በመስጠቱ ባንኩ ብድር ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ለተፈጠሩ ችግሮች የመሬት አሰጣጡ ችግር እንዳለበት አቶ ኢሳያስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መሬት ለአልሚዎች የሚቀርበው በሁለት መንገዶች ነው፡፡ የመጀመርያው የግብርና መሬት አስተዳደር ከክልሎች በውክልና የሚወስዳቸውን መሬቶች ለአልሚዎች ይሰጣል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ክልሎች በራሳቸው መንገድ ለአልሚዎች መሬት ያቀርባሉ፡፡

አልሚዎች ከእነዚህ አካላት የወሰዱትን መሬት ለማልማት አስፈላጊ መሥፈርቶች አሟልተው ሲቀርቡ ባንኩ ብድር ይሰጣል፡፡ በተደረገው ስብሰባ መልማት ላልቻሉ መሬቶች ተጠያቂ በሚሆነው አካል ማንነት ጉዳይ ላይ ሲሆን፣ ልማት ባንክ ለችግሩ ተጠያቂ የግብርና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ መሆኑን አመልክቷል፡፡

አቶ ኢሳያስ ከቀድሞ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ዲፕሎማ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቪርሲቲ በማኔጅመንት የመጀመርያ ዲግሪ፣ እንግሊዝ ከሚገኘው ዌልስ ዩኒቨርሲቲ በባንኪንግና ፋይናንስ ሁለተኛ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡

በሥራው ዓለም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ22 ዓመታት ከኦፊሰርነት እስከ ምክትል ፕሬዚዳንትነት የሠሩ ሲሆን፣ የኤቲኤም አሠራርን ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ እንዳስተዋወቁ ይነገርላቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደግሞ ለስምንት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የሠሩ ሲሆን፣ እሳቸው ሥልጣን ከያዙ ወዲህ የተበላሹ ብድሮች እየቀነሱ መምጣታቸውና የቦንድ ሽያጭ ማስጀመራቸው ከሚጠቀሱላቸው ለውጦች ውስጥ ናቸው፡፡
Source:Ethiopian reporter