Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ከኦነግ አመራሮች ተልዕኮ በመውሰድ በምዕራብ ወለጋ ዞን ሁከት ፈጥረዋል የተባሉ 22 ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው

img_0397

አዲስ አበባ፣ ህዳር 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኬንያና ኖርዌይ ከሚገኙ የኦነግ የሽብር ቡድን አመራሮች ተልዕኮ በመቀበል በምዕራብ ወለጋ ዞን በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሁከት በመፍጠር ጉዳት አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ 22 ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው።

ዛሬ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች 1ኛ ደረጀ አለሙ ደስታ፣ 2ኛ ተሾመ ድርብሳ፣ 3ኛ ባህሩ ሉጮ ጭብሳን ጨምሮ 22 ተከሳሾች ናቸው ክስ የተመሰረተባቸው።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው 1ኛ ተከሳሽ በ2006 ዓ.ም ወደ ኬንያ በመሄድ የሽብር ቡድኑ አባል በመሆንና የፓለቲካ ስልጠና በመውሰድ በ2008 ዓ.ም ለሽብር ማስፈጸሚያ 21 ሺህ ብርና አንድ ሲም ካርድ በማውጣት በሞያሌ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ይገባል።

አዲስ አበባ ከተማ ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 እና ወረዳ 04 ሃሰተኛ መታወቂያ በማውጣት ወደ ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ከተማ በመሄድ ከ13 እስከ 20ኛ ያሉ ተከሳሾች ጋር ይገናኛል።

በዚህ መልኩ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ከተማ በ5ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች ቤት በተለያዩ ጊዜያት በማረፍ በተለያዩ ቡድኖች በመደራጀት የሽብር መፈጸሚያ አካባቢዎችን ሲያጠኑ ቆይተዋል።

ኖርዌይ ሃገር የሚኖር ዶክተር ደገፋ አብዲሳ በተባለ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራር አማካኝነት ሶስት የሽብር ቡድን ታጣቂዎች እንዲቀበሉና እንዲያስተናግዱ በታዘዙት መሰረት ተቀብለው ከቡድናቸው ጋር እንዲቀላቀሉ አድርገዋል ይላል የአቃቤ ህግ ክስ።

በተጨማሪም ታህሳስ 5 ቀን 2008 ዓ.ም የብቅልቱ አንኮራ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ረብሻ እንዲያነሱ በማስተባበር የመሪነት ሚና እንደነበራቸው ክሱ ያስረዳል።

በእለቱ ከቀኑ 6 ሰአት ላይ የወረዳውን ፒካፕ መኪና የሰባበሩ ሲሆን፥ 25 ኩንታል የግለሰብ ጤፍ ማቃጠላቸውም በክሱ ተጠቅሷል።

በአጠቃላይ አቃቤ ህግ የመንግስትና የህዝብ ንብረት በማውደም፣ ለመፈጸም ማቀድ፣ ማዘጋጀትና ማሴር እንዲሁም በማነሳሳት የሽብር ወንጀል ነው ክሰ የመሰረተባቸው።

ተከሳሾቹ ቀደም ሲል በማረሚያ ቤት ሆነው ክሱ የደረሳቸው ቢሆንም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሲቃጠል ሳናነበው ተቃጥሎብናል፤ ክሱ ይሰጠን እንዲሁም ጠበቃ መንግስት ያቁምልን ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱም ክሱ ኮፒ ተደርጎ እንዲሰጣቸውና 1ኛ፣ 10ኛ እና 11 ተከሳሾችን ፖሊስ እንዲያቀርብ አዟል።

ክሱን ለመስማትም ለህዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።