አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አዲሱ ካቢኒ በባህሪው ልዩ እና መንግስት የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ይበልጥ ዝግጁ መሆኑን ያሳየበት ሆኖ አግኝተነዋል አሉ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የተለያዩ ዘርፍ ምሁራን።
በአዲሱ ካቢኒ ውስጥ መንግስት በፖሊቲካ ፓርቲ ብቻ ሳይታጠር የግለሰቦችን አስተዋጽኦ በሀገር ውስጥ ለማጉላት ያለውን ፍላጎት ተመልክተናልም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ትናንት ይፋ ካደረጉት የካቢኒ አባላት ውስጥ ሀያ አንዱ ለቦታው አዲስ እና ከዚህም ውስጥ ከሚኒስትርነት ደረጃ አንጻር መልካቸው አዲስ የሆኑ ግለሰቦች ታይተዋል።
ተሿሚዎቹ በአስርት የሚቆጠሩ ጥናታዊ ጽሁፎች በሙያቸው ማቅረባቸውና የተሾሙትም ከሙያቸው አንጻር መሆኑም ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ትምህርት ኮሌጅ መምህርና የሰብአዊ መብቶች የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ አቶ ሲሳይ መንግስቴ፥ የትናንቱ የካቢኒ ሹመት ላይ በፖሊቲከኛነት የሚታወቁ መልኮች አለመታየታቸው በልዩ ባህሪው እንዲነሳ ያደርገዋል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የፐብሊክ ፖሊሲ መምህር የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርህተስፋ በበኩላቸው፥ በችሎታ ወይንም ባለሙያዎቹ “ሜሪቶክራሲ” በሚሉት አሰራር ሚኒስትሮች መሾማቸው መልካም መሆኑን አንስተዋል።
የአሁኖቹ ሚኒስትሮች ህዝቡ ብዙ ጥያቄ እያነሳ ባለበት ጊዜ የመጡ ናቸው፤ ጥሩ ይሰራሉም ብዬ አስባለሁ ብለዋል ዶክተር ቆስጠንጢኖስ።
ሁለቱ ምሁራን በካቢኒ ውስጥ የታዩ ፊቶች ሁለት ነገርን ያሳየናል ይላሉ።
አቶ ሲሳይ በብዙ የሚኒስትርነት ቦታዎች የተሾሙት ግለሰቦች ከተሾሙለት ቦታ ጋር በትምህርትም በስራ ልምድም ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው መሆኑ እንደ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገራት በግለሰብ የሚታወቁ ፖሊሲዎችን በብዛት እንድናይ ይረዳናል ብለዋል።
ይህም ኢህአዴግ በተለምዶ ከምናውቀው ማእከላዊ አሰራር ለቀቅ ብሎ ለግለሰቦች ራሱን ክፍት ማድረጉን አሳይቶኛል ነው ያሉት።
የመንግስት ስልጣን ላይ ያለ ስራ መቀመጥ የማይቻልበት፣ እየተገመገሙ መውረድም አለ የሚል ነገር ማየታችን ደግሞ ሌላው ጉዳይ ብለዋል ዶክተር ቆስጠንጢኖስ።
ለትምህርት እና ለሙያ ብቃት በአዲሱ ካቢኒ ውስጥ ትልቅ ቦታ መሰጠቱ ከመልካም አስተዳደር ጀምሮ ህዝቡ ለሚያነሳችው ጥያቄዎች ምላሽን ይሰጣል ብለው እንደሚያምኑ ምሁራኑ ገልፀዋል።
ሆኖም ይህ ጅምር በመሆኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጤቱ ጎልቶ እንዲታይ አሰራሩ ታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ መውረድ አለበት ነው ያሉት አቶ ሲሳይ።
ሉላዊነት ወይንም ግሎባላይዜሽን ከበፊቱ በፈጠነ ጊዜ ፈጣን ምላሾችን የሚፈልጉ ችግሮችን ይዞ ይመጣል።
ስለዚህም ፈጣን የፖሊሲ ምላሽ የሚፈልጉ ጉዳዮች ሀገሪቱ ያጋጥሟታል ፤ በአዲሱ ካቢኒ ይህ ሊሳካ ይችላል የሚል እምነት አለኝም ብለዋል ዶከተር ቆስጠንጢኖስ።
መንግስት ለምሁራን የሰጠው ቦታ ከዚህም እንዲሰፋ እንፈልጋለን ያሉት ምሁራኑ፥ ሆኖም ለተቃዋሚ ፖሊቲካ ፓርቲ አባላትም ይህ ቦታ ይሰጥ፤ እነሱም ጋር በጎ ነገር አለ ብለዋል።