አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለ800 ሺህ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥሩ አራት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ /አግሮ ፕሮሰሲንግ/ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ወደ ስራ እንደሚገቡ ተነገረ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብርሃቱ መለሰ እንዳሉት በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብና ትግራይ ክልሎች የሚገነቡት ፓርኮች የዲዛይን ስራ የፊታችን ታህሳስ ይጠናቀቃል።
ከ250 እስከ 1 ሺህ ሄክታር ላይ የሚያርፉት ፓርኮቹ እያንዳንዳቸው ከ100 እስከ 300 ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ማስተናገድ ይችላሉ።
በፓርኮቹ ከሚገቡት ባለሀብቶች 80 በመቶው የሀገር ውሰጥ ባለሀብት ናቸው ተብሏል።
በአራቱ ክልሎች የሚገነቡት እነዚህ ፓርኮች በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚገነቡት 17 ፓርኮች መካከል ለማሳያነት እንዲሆኑ ለማሰቻል ነው የሚገነቡት።
ሚኒስትር ዴኤታው የልማት ባንክ 41 ቢሊየን ብር ለሊዝ ፋይናንስ መመደቡንና ይህ ገንዘብም በቀጥታ ለፓርኮቹ ይውላል ብለዋል።
የጣሊያን መንግስት 110 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፥ ደቡበ ኮሪያ ፕሮጀክቱን ለመደገፍ ቃል መግባቷ ተከትሎ የ268 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ቀርቦላታል።
ክልሎችም ከራሳችው በጀት የሚመድቡ ይሆናል ነው ያሉት ዶክተር መብርሃቱ።
በተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት የቴክኒክ ደጋፍ አስተባባሪው አቶ ጽጋቡ ተካ እንደገለጹት፥ ባለፈው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ በአራቱም ክልሎች የማህበረሰብ ግንዛቤ መፍጠር ስራ ተሰርቷል።
የኮርፖሬሽኖች ሞዴል ደንብ፣ መዋቅር፣ የስራ ሀላፊዎች የስራ ዝርዝር እና የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በባለቤትነት የሚመሩበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽኖችም ተቋቁመዋል ብለዋል።
ኮርፖሬሽኖቹ እንደ ንግድ ተቋም የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መመቻቸቱንም ነው አስተባባሪው የገለጹት።
አንድ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከአምስት በላይ ማቀነባበሪያዎች የሚኖሩት ሲሆን፥ ከ100 እስከ 300 ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን በውስጡ አካቶ መያዝ ይችላል።
ይህም አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ ለኢንዱስትሪ ማቅረብ ከማስቻሉም በላይ በጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ወጣቶችን በማደራጀት ውስን እሴት በመጨመር ለፓርኮቹ ማቅረብ የሚያስችላችው ይሆናል።
ፓርኮቹ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገቡ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ በሚደረገው ሽግግር ሚናቸው አብይ ነው ተብሏል።