አዲስ አበባ ፣ ህዳር 18 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በአመራር ደረጃ የጀመረውን ጥልቅ ተሃድሶ በማስፋት በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ እያስመዘገበ ያለውን ልማት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሣ ተክለብርሃን ተናገሩ።
“በጥልቀት በመታደስ ክልላዊና ሀገራዊ ህዳሴያችንን እናፋጥን” በሚል መሪ ሃሳብ 36ኛው የብአዴን የምስረታ በዓል ትናንት በድሬዳዋ በውይይት ተከብሯል፡፡
ውይይቱን የመሩት የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ካሳ ተክለብርሃን እንደተናገሩት፥ ብአዴን ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን ጠብቆ ከሌሎች እህት ብሔራዊና አጋር ድርጅቶች ጋር ሆኖ ባከናወነው ስራ በክልሉም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የልማት ስራ ተከናውኗል፡፡
በተለይ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ፣ ግዙፍ የመሠረተ ልማት አውታሮች እንዲስፋፉና ድህነትና ኋላቀርነትን ደረጃ በደረጃ እንዲቀንስ በማድረግ በኩል የመሪነት ሚናውን ተጫውቷል ነው ያሉት፡፡
የተገኙ ፍሬዎችን ለማስቀጠል ብአዴን በጥልቅ የመታደስ ጉዞ ከበላይ አመራሩ መጀመሩን ጠቁመው፥ ይህም የህዳሴ ጉዞውን ስኬታማ ለማድረግና ለህዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
በጥልቀት መታደሱ ድርጅቱ ከተነሳለት የህዝብ ወገንተኝነት ዓላማና የሀገሪቱን ዕድገት ከማስቀጠል ጋር የተያያዘ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ካሳ፥ ለሀገርና ለህዝብ የማይሰራ አመራር ቦታ እንደማይኖረው አስገንዝበዋል፡፡
በየደረጃው ያለው አመራር ለሀገር ዕድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት ሊሰራ ይገባል ያሉት አቶ ካሳ፥ ህዝቡም ሙስናን የሚጠየፍና የኪራይ ሰብሳቢነትን የመታገል ሃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቀጣይ ለድርጅቱ መስመር እንቅፋት የሆነውን ስልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል ተግባር በመከላከል የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት መሰራት ይኖርበታልም ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱልጀባር አብዱልሰመድ፣ ብአዴን በብዝሃነት ላይ ለተመሰረተው ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ለሕዳሴው ጉዞ እውን መሆን በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሶ ውጤታማ ድል ሲያስመዘግብ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡
እንደ ኢዜአ ዘገባ በቀጣይ የኪራይ ሰብሳቢነትና የጥፋት ሃይሎችን ሴራ በፅናት በመመከት ለድሬዳዋ ራዕይ ስኬት የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡